ዜና: መንግስት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት በፅኑ የሚያስፈልገውን እርቅ የበለጠ እንደሚያርቀዉ ስጋቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29/2014 –የኢትዮጵያ መንግስት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጡትና በወልቃይት ላይ ትኩረቱን ያደረገውን ሪፖርት ይዘት በጥንቃቄ እየመረመረ እንደሚገኝ ጠቁሞ የሪፖርቱ ስሜት ቀስቃሽ ተደርጎ መቅረብና የሚዲያ ዘገባ አቀራረብን መከተል የግኝቶቹንም ይዘትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባም መሆኑን አስታዉቋል። የሪፖርቱ ብሔር ተኮር ይዘትም መንግሥትን እነደሚያሳስበዉ፤ አንዱን ወገን ለማስደሰት በሚሞክርበት ጊዜ ውንጀላውን ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ የሚከፋፍል ይመስላል ብሏል መንግስት በመግለጫዉ፡፡ ይህ ምልከታ ጥላቻን በማቀጣጠል ጠንካራ ሃገርን ለመገንባት በፅኑ የሚያስፈልገውን እርቅ የበለጠ እንደሚያርቀዉም ስጋቱን ጠቁሟል፡፡

ዝርዝር መግለጫዉ የሚከተለዉ ነዉ
የኢትዮጵያ መንግስት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጡትና በወልቃይት ላይ ትኩረቱን ያደረገውን ሪፖርት ይዘት በጥንቃቄ እየመረመረ ይገኛል። ሪፖርቱ በሰብአዊ መብት ላይ የሚነሱ ከባድ ጥሰቶች ከሚባሉት በተጨማሪ በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰቱትንና በጥንቃቄ መታየት የሚገባቸውን የፖለቲካ ለውጦች፣ ሰላምና ደህንነት፣ የውስጥ ወሰን ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። የዘር ማጽዳት፣ የጦር ወንጀል እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ክስንም ያቀረበ ሪፖርት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙትን ሁሉ ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው። ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ፅህፈት ቤት የጋራ ምርመራ ዉጤቶችን ተከትሎ መንግስት የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ያቋቋመው። ግብረሃይሉ ዛሬ ባካሄደው ሁለተኛ ስብሰባ የምርመራ ሂደቱን ለማፋጠን የተለያዩ መመሪያዎችን አውጥቷል። የምርመራና ክስ የሚኒስትሮች ግብረ ሃይል ለአሁኑ ሪፖርትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በቅርበት ይመረምራል።ሁለቱ ተቋማት ጉዳዪን ለመመርመር የተጠቀሟቸውን በርካታ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክክለኛነት ላይ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል። በመጀመሪያ፣ የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸዉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ባላቸው አካላት ነው። እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የአንቂ ድርጅቶቹ ፍርድ መስጠት ብልህነት የጎደለዉ ነዉ። እንዲህ አይነቱ ሪፖርታቸው ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውልም የታወቀ ነው። ይህ አመለካከት ምርመራው በተገቢው ጥንቃቄ አለመፈፀሙን ከማሳየቱም በላይ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።የሪፖርቱ ብሔር ተኮር ይዘትም መንግሥትን ያሳስበዋል። አንዱን ወገን ለማስደሰት በሚሞክርበት ጊዜ ውንጀላውን ተመጣጣኝ ባልሆነ መንገድ የሚከፋፍል ይመስላል። ይህ ምልከታ ጥላቻን በማቀጣጠል ጠንካራ ሃገርን ለመገንባት በፅኑ የሚያስፈልገውን እርቅ የበለጠ ያርቀዋል።

የሪፖርቱ ስሜት ቀስቃሽ ተደርጎ መቅረብና የሚዲያ ዘገባ አቀራረብን መከተል የግኝቶቹንም ይዘትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባም ነው።በሌላ በኩል አንድን ቡድን ብቻ መውቀስ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለሰላም መስፈን አይበጅም። በሪፖርቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ድክመቶችም በግልፅ የሚታዩ ናቸው። ሪፖርቱ የተመሰረተዉ በአብዛኛው ለአንዱ ቡድን ቀረቤታ ባለቸዉ እማኞች ወይም ምስክሮች ላይ መሆኑም ሚዛናዊነቱን አስቶታል። የሪፖርቱ ጉልህ ድክመቶች እንደተጠበቁ ሆነው በሀገር መከላከያ ሰራዊትና በአማራ ልዩ ሃይል ላይ ፍትሃዊ ያልሆነ ዉንጀላ በሪፖርቱ ቢሰነዘርም የመንግስት የተዋቀረው ግብረሃይል በተገቢው መንገድ ምርመራ ያካሂድበታል።ይህ ሪፖርት መንግስት ለሰብአዊነት ሲባል ግጭትን የማቆም ዉሳኔን በመተግበር ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ባለው አቅም ሁሉ እየሰራ ባለበት ወቅት የወጣ ነው። በመንግስት በኩል የተወሰደዉ ይህ እርምጃ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት እውነተኛ መሰረት እንደሚጥልም ፅኑ እምነት አለዉ። ሪፖርቱ በሚያሳዝን ሁኔታ ለየትኛውም የሰላም ጥረት የማይጠቅሙ ምክረ-ሃሰቦችን ያስቀመጠ ቢሆንም መንግስት ሁሉንም የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን በጥልቀት በመመርመር የተገኘውን ውጤት ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.