ዜና: ሙስሊሙ ማህበረሰብ በትምህርት ቤት የሚደረጉ እገዳዎችን አወገዘ፣ የከተማው ትምህርት ቢሮ ትምህርት ከሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች የጸዳ መሆን አለበት ሲል ምላሽ ሰጥቷል

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዋና ሀላፊ ከትምህርት ቤቶች ጋር ባደረጉት ውይይት

መጋቢት 29፣ 2014፣ አዲስ አበባ:- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሙስሊም ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት የረመዳን ወር መጀመሩን ተከትሎ በርካታ ትምህርት ቤቶች ሶላት እና ሌሎች ተግባራትን በመከልከላቸው ብስጭታቸውንና ቁጭታቸውን እየገለጹ ነው።ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የስራ ኃላፊዎች እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ርዕሳነ መምህራን ባደረጉት ውይይት ትምህርት ከሀይማኖታዊ ተግባራት የፀዳ መሆን አለበት ተብሏል።

በዚህ ሳምንት የወጡ በርካታ ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት ብዙ ትምህርት ቤቶች ሙስሊም ተማሪዎች አሁን በተያዘው የረመዳን ወር የጸሎት ተግባራትን እንዳያከብሩ እና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ተማሪዎቹ ከክፍል እንዳይወጡ እየከለከሏቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ።ታዋቂው የሙስሊም ሊቅ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በሰጡት አስተያየት “ከሰሞኑ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ሊያውም በተከበረው በረመዳን ወር የተጀመረው ሰላትን ምክንያት በማድረግ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታቸው የማራቅ ዘመቻ ከጀርባው ማን እና ምን ይኖር ይሆን የሚለው የሁላችንም ጥያቄ ሆኖ ሰንብቷል።”  በማለት ተናግረዋል።

ኡስታዝ አቡበከር በመቀጠል በኢትዮጵያ ካለመረጋጋት ጀርባ ያሉትን ተግዳሮቶች እና  መንስኤዎቻቸውን ተራ ነዋሪዎች ለመተንተን ተገድደዋል ብሏል።”ካለመረጋጋቱ  በስተጀርባ “ምን ታስቧል?” የሚለው ጥያቄ የዕለት ተዕለት ጥያቄ እየሆነ መጥቷል” ያሉት ኡስታዙ ፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት “በጎ” ተብሎ ሊገለጽ እንደማይችል አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በትላንትናው እለት እንዳስታወቀው መጋቢት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በከተማው የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች እና የት/ቤት ርእሰ መምህራን መካከል በተካሄደው ውይይት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በሃይማኖት ሽፋን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን እና  ድርጊቱም ተማሪዎች የሚተዳደሩንትን ህግ የሚቃረን እና የሚጥስ እንደሆነ ተጠቅሷል። በውይይቱም አንዳንድ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ሃይማኖታዊ ተግባራትን የመፈፀም አዝማሚያ እንዳላቸው እና የፖለቲካ አጀንዳዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲመጡ በማድረግ ተማሪዎችን ወደ አላስፈላጊ ሁኔታዎች እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑም ተነስቷል።

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ እንደገለፁት “ ትምህርት ከሀይማኖታዊ ተግባራት የጸዳ ቢሆንም በአንዳንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይህንን በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን ያገኘው መርህ በመጣስ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተስተውለዋል ብለዋል። በሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች በትምህርት ሰአት ከግቢ እንዳይወጡ ርእሰ መምህራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። ቢሮው “ ትምህርት ከማንኛውም ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ የጸዳ እንዲሆን ከርዕሰ መምህራን ጋር ተስማምቻለሁ” ብሏል።

ከውይይቱና በኋላ ለወጡት ዜናዎች ምላሽ የሰጡት ኡስታዝ አቡበከር ሙስሊም ተማሪዎችን ሰላታቸውን እንዳይሰግዱ፣ እንዳይጾሙ እና ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ ለማድረግ የተበታተነ የሚመስል “የአስተዳደር ዘመቻ” የተወሰደ ይመስላል ሲል ስጋቱን ገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ መግለጫ አስመልክቶ ኡስታዝ አቡበከር ይህን ብለዋል “የሃይማኖት ነፃነትን የሚጋፋ፣ የሀገራችንን ህግና የሴኩላሪዝም መርህ አንሻፎ የተረጎመ፣ ወቅትና ሁኔታን ከግምት ያላስገባ የተሳሳተ አመራር እየተሰጠ እንደሆነ ያሳያል። በመሆኑም ተማሪዎችን፣ ወላጆችን እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በማሳተፍ ዛላቂ መፍትሄ የሚሰጥበት አካሄድ እንዲጀመር አጥብቄ እጠይቃለሁ። የተማሪዎችን የሃይማኖት ነፃነት የሚገፉ ጫናዎችም እንዲቆሙ እጠይቃለሁ። ሁሉም አካላት በስክነትና በምክንያት እንዲመሩም ጥሪዬን አቀርባለሁ።”

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ እንደገለጸው በመጪው ቅዳሜና እሁድ ትምህርት ቤቶች ከተማሪዎች ወላጆች ጋር በጉዳዩ ላይ ውይይት ይደረጋል ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.