ዜና: የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ ዞን የጦር ወንጀል እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል : ሂዩማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 28/2014 – የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች እና የሲቪል ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ምዕራብ ትግራይ ዞን ከህዳር 2020 ጀምሮ በትግራይ ተወላጆች ላይ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ፈፅመዋል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ መጋቢት 28 ይፋ ባደረጉት አዲስ ሪፖርት አስታውቀዋል። ሁለቱ አለማቀፍ የሰበአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የመንግስትን የዘር ማፅዳት ዘመቻ ደብቆ በመቆየት የክልሉን ተደራሽነት እና ገለልተኛ ምርመራ እንዳይካሄድ ገድቧል ብለዋል ።

ሪፖርቱ አክሎም በተለያዩ የምዕራብ ትግራይ ከተሞች የትግራይ ተወላጆች ለቀው እንዲወጡ የሚጠቁሙ ማስታወቂያዎች ታይተዋል ፣ የትግራይ ተወላጆች በ24 ሰዓት ውስጥ አከባቢውን ለቀው እንዲወጡ ወይም በ72 ሰዓታት ውስጥ እንዲገደሉ የሚሉ በራሪ ወረቀቶች እንደተበተነ ገልጿል። በምዕራብ ትግራይ ዞን የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ከአጎራባች የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች እና አጋሮቻቸው ጋር  የዘር ማጽዳት ዘመቻ ደርሷቸዋል ያለው ሪፖርቱ የግድያ፣ የአስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ እስር እና የግዳጅ ዝውውር ዘመቻ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው ሲል አትቷል።

የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና ሚሊሻዎች እነዚህን እኩይ ድርጊቶች እንዲያቆሙ፣ የሰብአዊ እርዳታ ኤጀንሲዎች ማቆያ ቦታዎች  እንዲደርሱ እና ለከባድ ወንጀሎች ተጠያቂዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተአማኒ የሆነ የፍትህ ጥረቶች እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረግ አለበት ሲሉ ሁለቱ አለማቀፍ የሰበአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሳስበዋል  ።

 ‘ከዚች ምድር እናጠፋችኋለን’ በሚል ርዕስ የወጣው ሪፖርት በምዕራብ ትግራይ አዲስ የተሾሙ ባለስልጣናትን ጨምሮ በአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች እና ፌደራል የጸጥታ ሀይሎች ተባባሪነት በምዕራብ ትግራይ ዞን በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና ብሔር ተኮር ወንጀሎች፣ ዛቻ፣ ህገወጥ ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ የጅምላ እስር፣ ዘረፋ፣ የግዳጅ ዝውውር ተፈጽሟል ፣ሰብአዊ እርዳታ በመከልከል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ከመኖሪያ ቤታቸው በዘዴ ተባረዋል ሲል አስነብቧል። እነዚህ በትግራይ  ህዝብ ላይ በሰፊው የተፈጸሙ ስልታዊ ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና የጦር ወንጀሎች እንደሆኑ ተጠቅሷል ። 

የሂዩማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር ኬኔት ሮት “ከህዳር 2020 ጀምሮ የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና የጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ለማስወጣት የዘር ማጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል” ብለዋል።የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብአዊ እርዳታ ተቋማት በአፋጣኝ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ወደ ክልሉ መድረሱን ማረጋገጥ፣ በግፍ የታሰሩትን ሁሉ መፍታት እና በደል የፈጸሙትን መርምሮ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ዳይሬክተሯ። አክለውም የጦርነቱ ተሳታፊዎች የሚደርጉት ማንኛውም ስምምነት በአፍሪካ ህብረት የሚመራ አለም አቀፍ የሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ምዕራብ ትግራይ ዞን በማሰማራት ሁሉንም ማህበረሰቦች ከጥቃት ለመጠበቅ ያስችላል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ አግነስ ካላማርድ በበኩላቸው “የኢትዮጵያ አለምአቀፍ እና አህጉራዊ አጋሮች አቋም በምዕራብ ትግራይ እየተፈጸመ ያለውን ወንጀል ከባድነት አላገናዘበም። መንግስታቱ የዘር ማፅዳት ዘመቻውን እንዲቀቆም፣ የትግራይ ተወላጆች በሰላምና በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ እና ለእነዚህ አሰቃቂ ወንጀሎች ፍትህ ለማግኘት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለባቸው ” ብለዋል። የምዕራብ ትግራይ ዞን በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኝ  ለም አካባቢ መሆኑን ያወሳው ሪፖርቱ በምዕራብ ትግራይ ላይ የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎች ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የወሰንና የማንነት ውዝግብ መነሻ መሆናቸውን አስታውሷል። ምእራብ ትግራይ በህዳር 2020 በትግራይ ግጭት በተቀሰቀሰ በሁለት ሳምንታት ውስጥ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በአማራ ክልል አጋር ሃይሎች እና ሚሊሻዎች ቁጥጥር ስር መውደቁንም አንስቷል።

በጦርነቱ መጀመርያ አከባቢ የኢትዮጵያ ፌደራልና አጋር ሃይሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል፤ ከነዚህም መካከል በከተሞች ላይ ከባድ መሳሪያ መተኮሱን እና ከህግ-ወጥ ግድያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ወደ ሱዳን ጎረቤት እና ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እንዲሰደዱ አድርጓልም ነው ያለው ሪፖርቱ።  የትግራይ ታጣቂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎችም ጥቅምት 30 ቀን ማይ ካድራ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው ጭፍጨፋ በአማራ ተወላጆች  ላይ የጦር ወንጀል መፈጽማቸውንም አስታውሷል።”በቀጣዮቹ ወራቶች በምዕራብ ትግራይ አዲስ የተሾሙ አስተዳዳሪዎች እና የአማራ ልዩ ሃይል፣ በክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች እና የመከላከያ ሃይል በመሆን በአካባቢው የትግራይ ተወላጆች ላይ የዘር ማጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።”

ከ15 ወራት በላይ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና የሂዩማን ራይትስ ዎች ተመራማሪዎች ከ400 በላይ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡ ወደ ሱዳን የተሰደዱ የትግራይ ተወላጆች በአካል በማግኘት የተደረገ ቃለ ምልልስ፣ በምዕራብ ትግራይ እና በአማራ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች እና የአማራ ክልል ተወላጆች፣ በደል የደረሰባቸው እና የአይን እማኞችን በማናገር እንዲሁም የህክምና እና የፎረንሲክ ሪፖርቶችን፣ የፍርድ ቤት ሰነዶችን፣ የሳተላይት ምስሎችን እና ከባድ የመብት ጥሰቶችን የሚያረጋግጡ የፎቶግራፍ እና የቪዲዮ ማስረጃዎችን ወቢ በማድረግ ያቀረቡት ሪፓርት እንደሚከተለው ይቀርባል።

 የዘር ማጽዳት ዘመቻ

የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች፣ ሚሊሻዎች እና አዲስ የተሾሙ ባለስልጣናት ከ2013 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ብሄርን መሰረት ያደረገ የማሳደድ ዘመቻ አካሂደዋል።

በተለያዩ የምዕራብ ትግራይ ከተሞች የትግራይ ተወላጆች ለቀው እንዲወጡ የሚሉ ምልክቶች ታይተዋል፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎችም የትግራይ ተወላጆችን እንዴት እንደሚያባርሯቸው  በግልፅ ስብሰባ ላይ ተወያይተዋል።በቤከር ከተማ የምትኖር  የትግራይ ተወላጅ ሴት ፋኖ በተባለው ኢ፟መደበኛ የአማራ ታጣቂ የደረሰባትን ዛቻ እንዲህ ስትል ተናግራለች።”ሁል ጊዜ ማታ ማታ ‘እንገልሻለን’…ከአካባቢው ውጪ’ ይሉ ነበር።”  የትግራይ ተወላጆች ከ 24 እስከ 72 ሰዓት ለቀው እንዲወጡ ካልሆነ ደግሞ እንደሚሞቱ የሚገልፅ በራሪ ወረቀቶች ተበትነው ነበር።” ስትል ምስክርነትዋን ሰጥታለች። 

ባለሥልጣናቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን በተጨናነቁ ቦታዎች ለረጅም ጊዜ እንዲታሰሩ እና እንዲንገላቱ  አድርገዋል።አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ዛሬም ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለው ያምናሉ።

የጸጥታ ሃይሎች በቡድን አስገድዶ መድፈርን፣የቃላት እና አካላዊ ጥቃትን፣ ጠለፋ እና ወሲባዊ ባርነትን ተጠቅመዋል። የ27 ዓመቷ የትግራይ ተወላጅ ሴት፣ ወንዶቹ ሲደፍሯት አንድ የሚሊሻ አባል “እናንተ የትግራይ ተወላጆች (ከተከዜ ወንዝ) በስተ ምዕራብ ካለ ምድር መጥፋት አለባችሁ። እናንተ ክፉ ናችሁ ስለሆነም ደማችሁን እናጸዳዋለን” እንዳሏት ተናግራለች።

የምዕራብ ትግራይ ባለስልጣናት የትግራይ ተወላጆችን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ከእንቅስቃሴ፣ ከሰብአዊ እርዳታ፣ ትግርኛ ቋንቋ ከመናገር እና የእርሻ መሬቶችን እንዳይጠቀሙ እገዳ ጥለዋል።የአማራ የጸጥታ ሃይሎች እና በአንዳንድ ቦታዎች የኤርትራ ሃይሎች በምዕራብ ትግራይ ተገኝተው ሰብል፣ ከብትና ቁሳቁስ በመዝረፍ የትግራይ ተወላጆችን ህልውና አደጋ ላይ ጥለዋል። የ63 ዓመቱ የአንድ መንደር አርሶ አደር በቡድን ሆነው ቤታቸውን ሲያወድሙ ተመልክተዋል። ከሰዎቹም አንዱ “ይህ የአንተ መሬት አይደለም። እዚህ ምንም የምትጠይቀው የለህም።” ሲል ለአዛውንቱ ተናግሯል። 

ብዙ የትግራይ ተወላጆች ረሃብ እና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው ሲሆን ከመውጣት ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም። በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ለማባረር በጭነት መኪና ወይም በአውቶብስ በመጫን  ወደ መሃል የትግራይ ክፍል ይልኳቸው ነበር።

ይህ የተቀናጀ ዘመቻ ለወራት የቀጠለ ነበር ።  በመጋቢት 2013 ዓ.ም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ተሰደዋል ወይም ተባርረዋል።በህዳር 2013 ዓ.ም የየጀመረው ማፈናቀል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በእድሜ የገፉ እና የታመሙ የትግራይ ተወላጆች፣ ወጣት እናቶች እና ህጻናት ሲባረሩ፣ የአማራ ሃይሎች ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎልማሶችን አስረዋል ለመሸሽ የሞከሩትን ተኩሰው ገድለዋል ።

የተከዜ ወንዝ ድልድይ እልቂት

ጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም ፋኖ የሚባሉ የአማራ ታጣቂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በብዘት የሚቆጠሩ የአዲ ጎሹ ከተማ ነዋሪ የሆኑትን ወንድ የትግራይ ተወላጆች ሰብስበው አስረዋል።

የአማራ ልዩ ሃይል አባላት ወደ 60 የሚጠጉ በጾታ ወንድ የሆኑትን የትግራይ ተወላጆችን ተከዜ ወንዝ ላይ በመሰብሰብ በጅምላ ረሽነዋል። ድርጊቱ ከዕለቱ አንድ ቀን በፊት የአማራ ሃይሎች ከትግራይ ሃይሎች ጋር ባደረጉት ውጊያ ከፍተኛ ኪሳራ ከደረሰባቸው በኋላ የበቀል ጥቃት ሊሆን እንደሚችል እማኞች እና በህይወት የተረፉት ጥቂቶች ተናግረዋል ።

“ጥይት ሲተኮሱብን መጀመሪያ ወደቅኩኝ ከዚያም ከፊት ለፊቴ የነበሩት ሌሎቹ በጥይት ተመተው ሲወድቁ አየሁ” ሲሉ በህይወት የተረፉት  የ74 ዓመት አዛውንት ተናግረዋል።”ከኋላዬ የነበሩት ሰዎች ደግሞ በላዬ ላይ ወድቀው ሸፈኑኝ…ከዛ በኋላ ‘የትግራይ ተወላጆች በቀላሉ አይሞቱም እንደገና ተኩስ’ ሲሉ ሰማሁ።” 

እልቂቱ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ከአዲ ጎሹ እንዲሰደዱ አድርጓል።

በእስር ቤት ውስጥ ሞት

በትግራይ ክልል በሚገኙ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የቀድሞ እስረኞች በአማራ ሃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች በሚተዳደሩ እስር ቤቶች በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ይናገራሉ። አንዳንዶቹ በደረሰባቸው ስቃይ፣ በህክምና መከልከል እና በምግብና በውሃ እጦት ህይወታቸው አልፏል፣ ጠባቂዎች ሌሎችን ገድለዋል። አንድ የ72 አመት አርሶ አደር “እነሱ [የአማራ ሚሊሻ  ጠባቂዎች] የትግራይ ተወላጆች በረሃብ መሞት እንደሚገባቸው ሲነግሯቸው እንደነበር” ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሃይሎችም ሆኑ የአማራ ባለስልጣናት በምዕራብ ትግራይ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ውንጀላዎችን አስተባብለዋል። የካቲት 18 ቀን 2014  አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያገኙትን ውጤት አስመልክቶ ለፌዴራል፣ ለአማራ እና ለትግራይ ክልል ባለስልጣናት ደብዳቤ ጽፈው ነበር። በወቅቱም ለደብዳቤው የአማራ ክልል መንግስት ብቻ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበር ሪፖርቱ ያትታል።

በመጨረሻም በትጥቅ ግጭት ሁሉም ወገኖች የአለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን  ወይም የጦርነት ህጎችን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ያሳሰበው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት፣ አለም አቀፍ እና የክልል አጋሮቹ በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ሁሉም ማህበረሰቦችን ለመጠበቅ በግፍ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆችን በአስቸኳይ መፍታት እና የጥበቃ ክትትል ማድረግን ጨምሮ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸውም ብሏል።   “በዚህም መንግስት በያዝነው አመት መጋቢት ወር ለሰብአዊነት ሲል  ተኩስ ማቆሙ ይታወሳል። ምንም ዓይነት እርቅ ወይም የተኩስ አቁም ቢደረግም፣ የኢትዮጵያ የፌዴራል እና የክልል ባለስልጣናት ያልተቋረጠ፣ ገለልተኛ እና ቀጣይነት ያለው ሰብአዊ እርዳታ ለተጎዱ እንዲዳርስ መፍቀድ አለባቸው።” ብሏል።  መንግስት በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ የሚሊሺያ ሃይሎችን፣ ፣የአማራ ልዩ ሃይል እና የኢትዮጵያ ፌደራል ሃይሎችን  በሙሉ  ትጥቅ ማስፈታት እና በከባድ በደል የተሳተፉትን ከስልጣን ማንሳት እንዳለበት አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች አሳስበዋል። “የምዕራብ ትግራይ ጊዜያዊ ባለስልጣናትን ጨምሮ የሲቪል ባለስልጣናት እና በከባድ በደል የተሳተፉ የጸጥታ ሃይሎች የምርመራ ሂደታቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ከስራ መታገድ አለባቸው” ብለዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.