ዮናታን ፍስሃ @YonatanFessha
አዲስ አበባ ሚያዝያ 27, 2012 – ኮቪድ-19 የሚያመጣው ተፅዖኖ በሕብረተሰብ ጤና ሥርዓቱ ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወረርሺኙ ስላለበት ሁኔታ ከዋና ዋና የዜና ማሰራጫዎች በየሰዓቱ የሚደርሰን መረጃ በቫይረሱ ምክንያት የተፈጠሩትን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ያሳያሉ፡፡ ቫይረሱ ሕገ መንግስታዊ ቀውስ የፈጠረበትን ሌላ አገር ግን ማሰብ አዳጋች ነው፡፡ ቢያንስ በርካቶች በኢትዮጵያ ያለውን የአስተዳደር ሁኔታ በዚህ መልኩ እየገለጹት ነው፡፡
በውጥረቱ መሃል ያለው ዋናው ጉዳይ አሁን ያለው አስተዳደር ከመስከረም 30 በኋላ የሥራ ዘመኑ ሲያበቃ እጣ ፈንታው ምን ይሆናል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡በመንግስት የቀረቡት አማራጮች በሕገ መንግስት ምሁራንና በፖለቲከኞች ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ አማራጮቹ ሰፊ እውቀና ከማግኘታቸው የተነሳ ስለሕገ መንግስቱ መነጋገር የኢትዮጵያውያን የትርፍ ጊዜ ሥራ ሆኗል ያስብላል፡፡
መንግስት ከፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉም ለመጠየቅ ወስኗል፡፡ መንግስት አመራጮቹን ካቀረበ በኋላ ውሳኔውን የወሰነበት ፍጥነት ግራ ያጋባል፡፡ ባለድርሻ አካላትን ትርጉም ባለው መልክ ለማሳተፍ የገባው ቃል ተዘንግቷል፡፡ ሆኖም ሕገ መንግስቱን በሚመለከት ያለው ውይይት ቀጥሏል፡፡
ፍፁም ማዕበል
ለኮቪድ-19 ምላሽ ለመስጠት መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ በፌደራልና በክልል ደረጃ ነሐሴ ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ምርጫ ተሰርዟል፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች ከሞላ ጎደል ከሁሉም የፖለቲካ መድረኮች ድጋፍ ያገኙ ይመስላል፡፡ነገር ግን በቀጣይ ምን ሊደረግ ይገባል የሚለው ላይ ስምምነት የለም፡፡ አሁን ያለው ምክር ቤት የሥራ ዘመን ሳያልቅ ምርጫ ባልተካሄደበት ሁኔታ ሕገ መንግስቱ ምን አይነት እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ ይሰጣል? ሕገ መንግስቱ ለዚህ ግልፅ መልስ የለውም፡፡
የሕገ መንግስት ዝም ሲል
አንዳንዶች ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ሕገ መንግስታዊ መፍትሄ የለም ማለት ነው ይላሉ፡፡ የሕገ መንግስት ዝምታ ሕገ መንግሰታዊ መፍትሄ አለመኖሩን የሚያመላክት ከሆነ የሕገ መንግስት ሰነዶች ሰፋፊና ረዥም ይሆኑ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የሕገ መንግስት ማሻሻያዎች በየጊዜውና ቶሎ ቶሎ ይደረጉ ነበር፡፡በመቶዎች ከሚቆጠሩ አመታት በፊት ባሪያዎች የነበሯቸው የአሜሪካ አባቶች ያዘጋጁት የአሜሪካ ሕገ መንግስት የተፈጠሩትን ለውጦች ተቋቁሞ እስከዛሬ መቆየት አይችልም ነበር፡፡ የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወሰነው ታሪካዊ ውሳኔ በዘር የተከፋፈሉ ትምህርት ቤቶችን ሕገ ወጥ ባያደርጋቸው ኖሮ ከ1960ዎቹም በኋላ ይቀጥሉ ነበር፡፡ የደቡብ አፍሪካ የሕገ መንግስት ፍርድ ቤት የሞት ቅጣትን ኢሕገ መንግስታዊ ባያደርገው ኖሮ አሁንም ወንጀለኞች በሞት ይቀጡ ነበር፡፡በካናደ የኪውቤክን መገንጠል በሚመለከት መንግስት ጠቀላይ ፍርድ ቤቱን ምክር ባይጠይቀው ኖሮ አገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ቀውስ ውስጥ ትገባ ነበር፡፡ ባጭሩ ‹‹ሕይወት ስላለው ሕገ መንግስት›› መነጋገር አንችልም ነበር፡፡
እውነታው ሕገ መንግስት ዝም ሲል ወይም አተረጓጎሙ ላይ ክርክር ሲነሳ በአለም ላይ ያሉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት የፍርድ ቤቶችን ምክር ይጠይቃሉ፡፡ ፍርድ ቤቶችና መሰል የዳኝነት አካላት አከራካሪም ቢሆኑ ክፍተቶችን በመሙላት ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ፡፡ይህ ማለት መንግስትና ፓርላማው ሕገ መንግስቱን ለመተርጎም ሥልጣን ከተሰጠው አካል (የፌደሬሽን ምክር ቤት) ሕገ መንግስታዊ ድጋፍ መጠየቃቸው ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ ዴሞክራሲን በሚከተሉ አገራት የተለመደ አሰራር ነው፡፡
ሕጋዊ ግን ተስማሚ ያልሆነ
ይህ አማረጭ ሕጋዊ ቢሆንም ተሰማሚ ግን አይደለም፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ዋናው ጉዳይ ደግሞ ሕገ መንግስቱትን ለመተርጎምም ሆነ ለማሻሻል የተቀመጠው ያልተለመደው ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠው ሥርዓት ነው፡፡
በሕገ መንግስቱ ፍርድ ቤቶች ሕገ መንግስታዊ ዳኝነት እንዳይሰጡ ተደርጓል፡፡ ሕገ መንግስቱንበሚመለከት የሚነሱ ክርክሮችን የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው ፖለቲካዊ አካል ለሆነው ለፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ በተለምዶ ምክር ቤቱ ብቸኛው ሕገ መንግስቱን የመተርጎም ሥልጣን ያለው አካል እደሆነ ይነገራል፡፡ የሕግ ባለሙያዎችንና ፖለቲከኞችን የያዘው የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ምክር ቤቱ ለሚቀርቡለት ክርክሮች ምላሽ መስጠት እንዲችል ሙያዊ ድጋፈ ያደርግለታል፡፡ የአጣሪ ጉባዔው ሚና ምክረ ሃሳቦችን በመስጠት ላይ የተገደበ ስለሆነ የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያስተላልፈው ምክር ቤቱ ነው፡፡ ይህ ያልተለመደ ሕገ መንግስትን የመተርጎም አሰራር ተዓማኒነት ያላቸውን በርካታ ባለድርሻ አካላት ስለማያሳትፍ በአገሪቱ ባለው ሕገ መንግሰቱን የመጠበቅ ሥራ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡
ምክር ቤቱ የፖለቲከኞች ስብስብ እንደመሆኑ ሕገ መንግስታዊ ዳኝነት የሚጠይቀው ሙያዊ ብቃት የለውም፡፡ ሕገ መንግስታዊ ክርክሮች ውስብስብ የሆኑ የሕግ ጥያቄዎችን ያስነሳሉ፡፡ በእርግጥ ይህ በኢትዮጵያ ሕግ አውጪዎች ዘንድ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ሕግ አውጪዎች ‹‹ውስብስብ የሆኑ የሕገ መንግስት ድንጋጌዎችን ይዘትና የሚያስከትሉትን ውጤት ለመተንተን›› ብቃት ሊኖራቸው የሚችልበት አጋጣሚ ጥቂት ነው፡፡ በእርግጥ ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባዔውን ድጋፍ ያገኛል፡፡ አጣሪ ጉባዔው ከሕገ መንግስቱ ጋር በተያያዙ በሚነሱ ክርክሮች ላይ ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ምክረ ሃሳቡን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ ምንም እንኳን የምክር ቤቱ የብቃት ውስንነት በአጣሪ ጉባዔው ተካክሷል ብሎ መከራከር ቢቻልም በሌላ በኩል ግን ምክር ቤቱ አጣሪ ጉባዔው ያገኛቸውን ግኝቶች ለማፅደቅ የተቀመጠ ደካማ ተቋም (rubber stamp) ያደርገዋል፡፡ ‹‹ምክር ቤቱ አጣሪ ጉባዔው የሚያቀርባቸውን ሪፖርት ከማጽደቁ ወይም ውድቅ ከማድረጉ በፊት ውይይት ሊያደርግባቸው ይገባል››፡፡ ይህ ደግሞ በእርግጠኝነት ሕገ መንግስታዊ መርሆችንና የሕግ ጉዳዮችን መፈተሽ ይጠይቃል፡፡ እስከዛሬ የነበረው ልምድ በማየት ምክር ቤቱ የዚህን ሙያዊ አካል ምክረ ሃሳብ ውድቅ ያደረገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በአጭሩ ምክር ቤቱ ሕገ መንግስቱን በተገቢው ደረጃ መጠበቅ የሚችል ብቃት ያለው፣ ገለልተኛና ተመራጭ አካል አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ምክር ቤቱ ጋር ጥቂት ጉዳዮች ብቻ መቅረባቸውና አብዛኛዎቹ ውሳኔዎች ደግሞ ለመንግስት የሚያደሉ መሆናቸው የሚያስገርም አይደለም፡፡ ምክር ቤቱ ያሉበት ተቋማዊና የአሰራር ችግሮች ተቋሙ ሕገ መንግስታዊነትን ማዳበርና ውጤታማ የፌደራል አስተዳደር መገንባት እንዳይችል አድርገውታል፡፡ ስለዚህ የገጠመንን ሕገ መንግስታዊ እንቆቅልሽ ምክር ቤቱ ይፈታዋል ብሎ መተማምን አዋጭ አይደለም፡፡ ሆኖም ከሕገ መንግስቱ ውጪ መፍትሄ ማፈላለግ አለብን ከሚለው አማራጭ አይብስም፡፡
‹‹ሕገ መንግስቱን ወደጎን መተው››?
ሕገ መንግስቱን በመተው ይህን ጉዳይና ይህን ጉዳይ ብቻ በሚመለከት ስምምነት ላይ መድረስ የሚለው ሃሳብ በስፋት እየተነገሩ ካሉት አስተያየቶች ውስጥ አንዱነው፡፡ ነገር ግን ይህ አስተያየት የሕገ መንግስቱንየማሻሻያ ሂደት የሚመራ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት የቀረበ ጥያቄ አይደለም፡፡ ምናልባት አላማው ሕገ መንግስቱ ሳይነካ አገሪቱን ለሚቀጥለው ምርጫ የሚያዘጋጅ የሆነ አይነት አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ከሕገ መንግስቱ ውጪ ለመንቀሳቀስ የቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ የቀረበው ክርክር ይህን የምናደርገው ለተወሰነ ዓላማብቻ ስለሆነ ችግር እንደሌለው ያስረዳል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥሪ መንግስት እንዴት መመስረት እንዳለበት የሚደነግገውን የሕገ መንግስቱን የተወሰነ ክፍል ለማገድ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 9 ላይ ‹‹በሕገ መንግስቱ ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው›› የሚለውን ድንጋጌ ወደ ጎን ለመተው የቀረበ ሃሳብ ነው፡፡ ይህ ግን የማይሆን ነው (one cannot have the cake and eat it too)፡፡ ወይ ሕገ መንግስቱ በሚያስቀምጣቸው ገደቦች ውስጥ መንቀሳቀስ ነው ወይ ደግሞ ሕገ መንግስቱን ሙሉ በሙሉ በመተው በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ሌላ ማህበራዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድር ማድረግ ነው፡፡
የወደፊት አቅጣጫ
ከፌደሬሽን ምክር ቤት እገዛ ማፈላለግ ፖለቲካዊ ችግር ያስከትላል፡፡ ነገር ግን ጠንካራ የሆነ ሕገ መንግስታዊ መሰረት አለው፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ ከሕገ መንግስቱ ውጪ መሄድ ሳይሆን የቀረበው ሃሳብ ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ ማፈላለግ ነው፡፡ አሁን ከባድ የሆነው የምክር ቤቱና የአጣሪ ጉበዔው ሥራ ይሄው ነው፡፡ምናልባት በዚህ ጉዳይ ምክር ቤቱ የአጣሪ ጉባዔውን ምክረ ሃሳቦች ለመቀበል ፖለቲካዊ ውሳኔ መወሰን አለበት፡፡ ከዚያም አጣሪ ጉባዔው ሆን ብሎ አሁን ያለው መንግስት ሥልጣኑን እንዲያራዝም ፈቃድ ሰጥቶ ብቻ ዝም በማለት እንደማያስገርመን ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ ይልቁንም ቀጣዩ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን ማስተዳደር የሚቻልበትን አሰራር የሚያመላክት ሌሎች ጉዳዮችን የማይነካ መመሪያም ቢያዘጋጅ መልካም ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ተፎካካሪዎቹን ለመብለጥ ያላግባብ መንግስታዊ ተቋማትን በመጠቀም ለምርጫው የሚያግዙትን ሁኔታዎች እንዳያመቻች ሕገ መንግስታዊ መርሆችን ሊያስተዋወቅ ይገባል፡፡
የኤዲተር ማስታወሻ፡ ዮናታን ፍስሃ በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግስት መምህር ሲሆኑ በሚቀጥለው አድራሻ ሊገኙ ይቻላል፡-yfessha@gmail.com