ዜና፡ የማላዊ ፖሊስ 72 ኢትዮጵያውያንንማሰሩን ገለጸ፤ መንግስት 25 ኢትዮጵያዊያን በማላዊ ሞተው ተገኝተዋል የተባለውን ጉዳይ እያጣራው ነው አለ

በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ በማዕከላዊ ክልል የሚገኘው የማላዊ የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት መምሪያ 114 የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው እየመለሰ መሆኑን አስታውቋል። ፎቶ፡ ማላዊ24

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም – የማላዊ ፖሊስ በማላዊ ሰሜናዊ ግዛት በምትገኘው ካሮንጋ ዉስጥ በሚገኝ ጥብቅ ደን ውስጥ ተደብቀው የተገኙ 72 ኢትዮጵያውያንን ማሰሩን ገለጸ፡፡ በተጨማሪም አሥር የማላዊ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማዘዋወር እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ፖሊስ አክሏል።

ከሁለት ቀናት በፊት የማላዊ ፖሊስ የኢትዮጵያውያን ሊሆን ይችላል ያለውን የ25 ስደተኞች አስከሬን የያዘ የጅምላ መቃብር ማግኘቱን አስታውቆ ነበር፡፡

“መቃብሩ የተገኘው ማክሰኞ ረፋድ ላይ ቢሆንም አስክሬኖቹን ማውጣት የጀመርነው ዛሬ ነው። እስካሁን 25 አስከሬኖች አግኝተናል” ሲል የፖሊስ ቃል አቀባይ ፒተር ካላያን መግለፁን AFP ዘግቧል። እንደ ሪፖርቶቹ ከሆነ ፖሊስ ሟቾቹ በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ እየተጓጓዙ እንደነበር ግምቱን ገልጧል።

ይህ በእዲህ እንዳለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው አጭር መግለጫ 25 ኢትዮጵያዊያን በማላዊ ሞተው ተገኝተዋል በሚል የተሰራጨውን ዘገባ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመሆን እያጣራ መሆኑን አሳውቋል። አደጋው አሁንም የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውርን አስከፊነተ የሚያሳይ ነው ያለው መግለጫው ሟቾቹ ኢትዮጵያዊያንም ሆኑ ሌሎች አፍሪካዊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሀዘን ተሰምቶታል ብሏል።

በማላዊ ሰሜናዊ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ደን ውስጥ ተደብቀው የተያዙት እነዚህ 72 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጅምላ መቃብሩ ከተገኘበት 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑ የማላዊ ፖሊስ ገልጿል። አክሎም 72ቱ ኢትዮጵያውያን እና አሥሩ የማላዊ ዜጎች ከሰሞኑ ፍርድ ቤት ቀርበው ከሰው ዝውውር እና የስደተኞች ሕግጋትን መተላለፍ ጋር የተያያዙ ክሶች  እንደሚቀርብባቸው ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል

እንደ ማላዊ24 ዘገባ የሰሜን ክልል ፖሊስ ከጥር እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ 221 ስደተኞችን መያዙን ገልጿል፤ ከነዚህም ውስጥ 186ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል።

ባሳለፍነው አመት ሰኔ ወር ላይ አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በመሆን ባደረጉት ማጣራት በማላዊ የነበሩ ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው የጉዞ ሰነድ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተሰጥቷቸዋል።

የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንደገለፀው ማላዊ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚወስደው የየብስ መስመር ላይ የምትገኝ ሀገር ስትሆን በዋናነት ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ የመጡ ያልተመዘገቡ ስደተኞች እስከ ኬፕታውን ድረስ የስራ እድል ለማግኘት እንደ መተላለፊያ ይጠቀሙበታል።

በ2008 ዓ.ም.  ድንበር የለሽ ዶክተሮች እንደገለፀው  አብዛኛዎቹ  ከኢትዮጵያ የመጡ ከ200 የሚበልጡ ስደተኞች ፤ ህጋዊ ሰነድ ስለሌላቸው በአሁን ጊዜ በማላዊ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። “አብዛኞቹ ወደ ደቡብ አፍሪካ በመጓዝ ላይ ነበሩ” ሲል የህክምና በጎ አድራጎት ድርጅቱ ገልጿል። ስደተኞቹ አብዛኛውን  ጊዜ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ታስረው ይቆያሉ። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.