ዜና፡ በትግራይ ክልል 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 29፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም በትግራይ ክልል በኮቪድ 19 እና በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከ2012 ጀምሮ ተቋርጦ የቆየው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር እሸቱ ከበደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በታቀደው ግዜ ፈተናውን ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት መስፈርቱን የሚያሟሉ ተፈታኞች ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር የፈተና ዝግጅት፣ የሎጅስቲክስና ሌሎችም ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ ክልል የአጠቃላይ ትምህርት ሁኔታ ወደ መደበኛ ሂደት መግባቱን መናገራቸው ይታወቃል።

በዚህም በክልሉ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለፈተና ለማዘጋጀት የተፋጠነ የትምህርት አሰጣጥ መተግበሩን ተናግረዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም መምህራንን እየጠሩ ነው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በበኩሉ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ለፈተና የሚያበቃ የማጠናከሪያ ትምህርት እየወሰዱ ይገኛሉ ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.