ዜና: የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል የነበርው ጦርነት እንዲቆም ጥረት ባለማድረጉ ይቅርታ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29/ 2015 ዓ.ም፡- የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በትግራይ ክልል በነበርው ጦርነት ወቅት ቅድስት ቤተክርስቲያን ጦርነቱ እንዲቆም መግለጫ ባለመስጠቷ ፣ በጦርነቱ መካከል ወደ ትግራይ ክልል መግባትና መውጣት በሚቻልበት ወቅትም በክልሉ የሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና መላው ሕዝበ ትግራይን በአካል በቦታው ተገኝታ ባለመጠየቋና ባለማጽናናቷ ይቅርታ ጠይቋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ በዋጣው መግለጫ ጦርነቱ ቆሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እርቀ ሰላም ከወረደበት ጀምሮ ለደረሰው ጉዳት በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ በውሳኔው መሠረት በወቅቱ ማድረስ ባለመቻሏ ፣ በዚሁም የተነሣ በቤተ ክርስቲያኗና በመላው ሕዝበ ትግራይ መካከል ለተፈጠረው ቅሬታና አለመግባባትም  ቅዱስ ሲኖዶስ ይቅርታ ጠይቋል።

ይህ በእንዲህ እያለ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ የልዑካን  ቡድን ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም  ወደ ትግራይ  ርዕሰ ከተማ መቐለ እንደሚጓዝ የኢኦተቤ ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ 13 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ .ም ወደ ክልል ትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ይጓዛል ብሏል።

ልዑካን ቡድኑ ወደ መቐለ የሚጓዘው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ የተወሰነውን ሰብአዊ  ድጋፍ ለማድረስና በትግራይ ከሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር  መሆኑ ተገልጧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.