ዜና፡ አሜሪካን እና ብሪቴንን ጨምሮ አምስት ሀገራት በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች የሚታየው በሀይል የታገዘ ጥቃት አሳስቦናል ሲሉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5/2015 ዓ.ም፡- የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራልያ፣ ጃፓን እና ኒውዝላን መንግስታት በጋራ ባወጡት መግለጫ  ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች የሚታየው ሀይል የታገዘ ጥቃት በክልሎቹ አለመረጋጋት መፍጠሩ እና ንጹሃንን መቅጠፉ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።

ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ ሁሉም ተፋላሚ ሀይሎች ንጹሃንን እንዲታደጉ፣ ሰብዓዊ መብትነ እንዲያከብሩ እና ውስብስበ የሆኑ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል። አለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያውያን ዘላቂ ሰላማቸውን ለማረጋገጥ ለሚያደርጉትን ጥረት አሁንም ድጋፉን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሀገራቱ የጋራ መግለጫ መንግስት እና ታጣቂ ሀይሎች ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተሰሙ ያሉ ድምጾች መበራከት ማሳያ ነው። በትላንትናው እለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ዓለም አቀፍ ኮሚሽን የኢትዮጵያ መንግሥት በሕግ ማስከበር ሥራው ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማሳሰቡ ይታወሳል።

የህጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) በመንግስት ፀጥታ ሀይልና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት በተቀሰቀሰበት አማራ ክልል ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል። “በቅርቡ የተደረገው ጦርነት ያስከተለው ቁስል ጠባሳ ሳይሻር አሁንም ተደግሟል፤ የህፃናት ህይወት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ሰብዓዊ ድርጅት ተፋላሚ ፓርቲዎች ለንፁሃን ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡና በክልሉ የሚገኙ 580 ሺህ ተፈናቃዮችን ጨምሮ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የስብኣዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲደርሳቸው እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ህፃናትን ከረሃብ፣ ከግጭት፣ መፈናቀልና ጥቃት መጠበቅ አለብን፡፡ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ቤተሰቦች ደህንነታቸው እንዲጠበቅላቸው እና አስፈላጊ ሰብአዊ እርዳታን ያለ ምንም እንቅፋት እንዲያገኙ ማድረግ አለብን” ሲሉ በኢትዮጵያ የህጻናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ዣቪየር ጆበርት ገልፀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመራ፣ በአጭር ግዜ እንዲያልቅ፣ አዋጁን ለማስፈፀም የተሰማሩ አካላትም ከማንነት ተኮር ፍረጃዎች፣ ወከባዎች፣ ዘፈቀደ እስራትና አካላዊ ጥቃቶችን ባለመፈጸም እንዲሁም በየትኛውም አካል እንዳይፈጸሙ ጥበቃ የማድረግ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መጠየቁንም የተመለከተ ዘገባ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅታዊ መረጋጋት እንጂ ዘላቂ ሀገራዊ ሠላምን የሚያመጣ መንገድ ሰላልሆነ መንግሥት በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ውይይት እና ሰላማዊ መፍትሔን በማስቀደም ችግሩን ለመፍታት በሙሉ ልብ እንዲሠራ ሲል ማሳሰቡም ተዘግቧል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.