ዜና፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመራ፣ በአጭር ግዜ እንዲያልቅ አብን ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3 /2015 ዓ.ም፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመራ፣ በአጭር ግዜ እንዲያልቅ፣ አዋጁን ለማስፈፀም የተሰማሩ አካላትም ከማንነት ተኮር ፍረጃዎች፣ ወከባዎች፣ ዘፈቀደ እስራትና አካላዊ ጥቃቶችን ባለመፈጸም እንዲሁም በየትኛውም አካል እንዳይፈጸሙ ጥበቃ የማድረግ ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠየቀ፡፡

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ነሃሴ 3 ቀን ባወጣው መግለጫ የፌደራሉ መንግስት ህዝባዊ የውይይት መድረኮችም እንዲፈጠሩ፣ ህዝቡም የሰላም ጥረቶችን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርቧል።

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የማይጠበቅ ክስተት አልነበረም ያለው አብን “በክልሉ የተከሰተው ችግር ዋነኛ ማጠንጠኛ የመንግስታዊ ስርዓቱ እና የክልሉ የአመራር ክፍተትና ብልሽት ነው” ሲል ከሷል፡፡ አብን በቀጣይ ማህበረሰቡን የሚመጥን እና በማህበረሰቡ የሚታመንበት አደረጃጀት በየደረጃው ተመስርቶ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ተቆጥረው ግልጸኝነት እና መተማመን እንዲፈጠርባቸውና ተቋማዊ በሆነ አግባብ ምላሽ እንዲያገኙ እንዲደረግ አሳስቧል፡፡

ፓርቲው አክሎ በመግለጫው በየትኛውም አሰላለፍ እና አግባብ ስለአማራ ህዝብ የተሰለፉ ሀይሎች ጦርነት ዘላቂ ጥቅምን ለማረጋገጥ አስቻይ ባለመሆኑና ይልቁንም ህዝብን ለተደራራቢ የማህበራዊ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ድቀት ስለሚዳርግ ለሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄዎች ተገቢውን ስፍራ ሰጥተው ለክልሉ ሰላም መመለስ ታራካዊ ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

“የአማራ ህዝብ ከሌላው የሀገሪቱ ህዝብ ጋር ያለውን የወንድማማችነት እሴቶች ከሚንዱ ቅስቀሳዎች፤ በራሱ እና በልጆቹ የተመሰረቱ ተቋማትን በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሚያጠለሹ መልዕክቶች እንዲሁም የአማራ ህዝብ ማህበራዊ ረፍት እንዲያጣ ከሚመኙ አካላት በስልት የሚሰጡትን አጀንዳዎች በመጸየፍ ወደ ሰላም መድረክ የሚያመሩ መንገዶችን ሁሉ ለመጥረግ አቅሙ የፈቀደውን ርብርብ እንዲያደርግ በአደራ ጭምር እናሳስባለን” ብሏል ፓርቲው።

በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም መደፍረስ የክልሉ መንግስት ብቃት ማነስና ወካይ አለመሆን ያስከተለው ምስቅልቅልም ነው ሲል የገለፀው አብን የአማራ ልሂቃን እና የፖለቲካ ሀይሎች እንዲሁም የተለያዩ የሲቪክ አደረጃጀቶች የራሳቸው ድክመት እንዳለ ሁሉ የክልሉ መንግስት እነዚህ አካላት በጋራ እንዳይመክሩና መፍትሄ እንዳያፈላልጉ በስልት መድረክ መነፈጋቸው ተደማሪ ችግር ሆኖ መቆየቱ እንደሚያምን አስታውቋል፡፡

ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ለእስር የተዳረጉ ሰወች ጉዳያቸው በአስቸኳይ ወደ ህግ ቀርቦ እንዲጣራና ተገቢው መፍትሄ እንዲሰጣቸው እና የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚያገኙ በአደባባይ ዋሰትና እንዲሰጥ አብን አበክሮ ጠይቋል፡፡

“በተቻኮለ የአደረጃጀት ለውጥ ምክንያት የተበተነውን ልዩ ሀይል” እና “በህልውና ትግሉ ውስጥ አስተዋጽኦ የነበራቸው” ያላቸውን  የፋኖ አባላት በተመለከተ የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስት የጋራ ኃላፊነት ወስደው በሀቀኛ ውይይቶች ላይ የተመሠረተ የሁለቱንም አካላት ክብርና አበርክቶ የሚመጥን መርሀ-ግብር በአስቸኳይ በመንደፍ ገቢራዊ ስራ እንዲሰሩ ሲል ጠይቋል።

አሁን በክልሉ ለተፈጠረው አጠቃላይ የጸጥታ መደፍረስ፣ ለደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ መንግስት ኃላፊነት እንዲወስድ እና ህዝቡን ይቅርታ እንዲጠይቅ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

የወልቃይትና የራያ ጉዳይ ግልጽ መፍትሄ አለማግኘቱ፣ ፍትሃዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ጥያቄ፣ ፍትሃዊ የበጀት ክፍፍል ጥያቄ ፣ የአርሶአደሩ የማዳበሪያ ጥያቄ፣ ገበሬው ያመረተውንም ወደገበያ እንዳይወስድ ተደጋጋሚ የመንገድ መዘጋትና መስተጓጎል ወዘተ ጉዳዮች በቂ መንግስታዊ ትኩረት ሳያገኙ መቆየታቸው ህዝባችንን ለከፍተኛ ምሬት ዳርገውታል ያለው መግለጫው በዚህም የተነሳ ለአፍራሽ ፕሮፓንዳ እና ለከፍተኛ ጥርጣሬ ጭምር እንዲጋለጥ አድርገውታል ብሏል።  መንግስት በነዚህ ጉዳዮች ከህዝብ ጋር ግልጽ ውይይት በማድረግ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ፓርቲው አሳስቧል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.