ዜና፡ “በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ፈተና ሲሰጥ የነበረ አንድ መምህር እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባሎች ተገድለዋል”- ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29/2015 ዓ.ም፡- በመከላከያ ሀይል እና ኢመደበኛ ኃይሎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመስጠት ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈታኝነት ተመድበው የሄዱ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተግባቦት መምህር የነበሩት ታደሰ አበበ ገብረሀና (ረ/ፕ/ር) እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባሎች መገደላቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡  

ባለትዳርና የ3 ሴት ልጆች አባት የነበሩት መምህሩ የተገደሉት ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ/ም መሆኑን ሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ትላንት በሰጠው መግለጫ ገልጧል፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር በመግለጫው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪ ፣ ፋሲል እና ቴዎድሮስ በተባሉ ሶስት ካምፓሶች ላይ ሐምሌ 27 ባጋጠመ ችግር 16 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይፈተኑ ቀርተዋል  ሲል ገልጧል፡፡ ተቋሙ ተማሪዎቹ በቀጣይ በሚመቻች መርሐ-ግብር ይፈተናሉ ብሏል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ካጋጠመው ችግር ውጪ በአማራ ክልል በሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠው ፈተና በሰላም ነው የተጠናቀቀው ያለው ተቋሙ በአማራ ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይም የአውሮፕላን በረራ በተቋረጠባቸው አካባቢዎች ያሉ የፈተና አስፈጻሚዎች ሁኔታው እስከሚረጋጋ ድረስ ትንሽ ቀን መጠበቅ አለባቸው ሲል አሳስቧል፡፡

በጋምቤላ የተወሰኑ ተማሪዎች ባጋጠማቸው ሕመም 38 ተማሪዎች ፈተና አለመውሰዳቸውንና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎና ልደታ ካምፓሶች እንዲሁም በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የገቡ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው ተቧድነው በፈጠሩት ፀብ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል።

ተቋሙ በመግለጫው በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የነበሩ ተማሪዎች በቡድን ሆነው ተማሪዎችን ከማስፈራራት እና ከመስረቅ ባሻገር የተማሪዎችን የመኝታ ቤት በር እና መስታወት እንዲሁም የተማሪ ሎከር ሰብረዋል ሲል ጠቅሶ ተቋማቱ 87 ተማሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ብሏል። ከነዚህ ውስጥ 49 ያህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ ከተፈጸመው ድርጊት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው ተብሏል።

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 840,859 ተማሪዎች መፈተናቸውና “ፈተናው ከስርቆትና ከኩረጃ ነጻ ሆኖ መጠናቀቁን” የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.