ዜና፡ በዴንማርክ የነበሩ ሁለት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ጥንታዊ የግዕዝ መድብሎች ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

በ16ኛው ክ/ዘመን የተጻፈ አንድ የግዕዝ መዝሙረ ዳዊትና አንድ የግዕዝ መልክዓ-ማርያም የግል የፀሎት መፅሐፍ፡፡ ፎቶ፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2015 ዓ.ም፡- በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሲውዲናውያን ቤተሰቦች ሁለት ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የብራና የፅሑፍ ቅርሶችን ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ገለጠ፡፡

በ1950ዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይኖሩ ከነበሩ ሲውዲናውያን ቤተሰቦች አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ክርስትል ዌስትላንድ ሃርቡ ባለቤታቸው ከኢትዮጵያ ወደ ዴንማርክ ይዘውት የወጡትን በፅሑፍ አጣጣሉ በ16ኛው ክ/ዘመን የተጻፈ አንድ የግዕዝ መዝሙረ ዳዊትና አንድ የግዕዝ መልክዓ-ማርያም የግል የፀሎት መፅሐፍ በራሳቸው ተነሳሽነት ለሲውዲሽ የወዳጅነት ማህበር አስረክበዋል ሲልም ባለስልጣኑ ጨምሮ ገልጧል ፡፡

ከተቋቋመ 70 ዓመታን ያስቆጠረውን የሲውዲናውያን የወዳጅነት ማህበርን ላለፋት ስድስት ዓመታት በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኢትዮጵያዊው ሲውዲናዊው ዶ/ር ቢንያም ወንድሙ እራሳቸው ቅርሱን ወደ ሃገር በማምጣት ለኢትዮጵያ የቅርስ ባለሥልጣን አስረክበዋል፡፡

ዛሬ ታህሳስ 26 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በተደረገው የቅርስ ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የሲውዲናውያን የወዳጅነት ማህበር ሊቀመንበር በዶ/ር ቢንያም ወንድሙ እና በኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) መካከል የቅርስ ርክክብ ተከናወነ፡፡

በቅርስ ርክክብ ሥነ-ሥርአቱ ላይ የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን ና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) ከሀገር የወጡ ቅርሶች ለማስመለስ የተደረገውን ጥረቶችን አስመልክተው ሲናገሩ “ባለፉት ዓመታት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር በመተባባር በተለያዩ ጊዜ ከሀገር የወጡ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ እንደነበረ ጠቁመዋል”፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም ዘንድሮም ብሔራዊ ኮሚቴውን በማጠናከር የተሻለ የቅርስ ማስመለስ ስራ እንዲያከናውኑ የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በዕለቱ በቅርሱ መመለስ በየደረጃው የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት በአቶ አበባው አያሌው (ረ/ፕ/ር) የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ቅርሶቹን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት አካላት በሙሉ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን እና በራሳቸው ስም ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አስ

ለተጨማሪ መረጃ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.