ዜና፡ በደብረ ብርሃን መጠለያ ካምፖች ውስጥ ከ116 በላይ ተፈናቃዮች በኩፍኝ በሽታ መያዛቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2015 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በደብረ ብርሃን ከተማ ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ወይንሸትና ቻይና መጠለያ የመጠለያ ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ሃላፊዎችን ዋቢ አድርጎ ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎቹ የኩፍኝ በሽታ በመከሰቱ ተፈናቃዮች እየተጠቁ መሆናቸውን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት መምርያ ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በተፈናቃዮች ላይ የተከሰተውን የኩፍኝ በሽታ ለመከላከል የጤና አገልግሎት ሠራተኞች ርብርብ እያደረጉ እንደሆነ ኃላፊው አክለው አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምርያ ኃላፊና የተፈናቃዮች አስተባባሪ አቶ በየነ ሳህሉ በበኩላቸው፣ከሁለት ሳምንት ወዲህ በሁለቱም ካምፖች የኩፍኝ በሽታ መከሰቱን አረጋግጠው፣ ዘገባው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ116 በላይ ተፈናቃዮች መጠቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመጠለያ ጣቢያዎቹ ከፍተኛ የምግብ እጥረት በማጋጠሙና ተፈናቃዮች በሽታውን ለመቋቋም አቅም ስላነሳቸው በሽታው ሊከሰት መቻሉን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ደረጀ ይነሱ በበኩላቸው፣ መንግሥት በየወሩ ድጋፍ ማድረግ ቢኖርበትም ዕርዳታው በየወሩ እየደረሰ እንዳልሆነ፣ ለአብነትም ተፈናቃዮቹ በዓመት ውስጥ ያገኙት የሦስት ወራት ድጋፍ ብቻ መሆኑንና ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰቱን አስረድተዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በማኅበረሰቡ ውስጥ ነው ተጠልለው የሚገኙት፤›› ያሉት አቶ ደረጀ፣ በዞኑ በሚገኙ 17 የመጠለያ ካምፖች ብቻ ከ90 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉና ሁሉም ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ከ146 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ውጪ ማኅበረሰቡ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሸገር ከተማ ቤት ፈርሶባቸው ወደ ዞኑ በመሄድ ወደ መጠለያ ካምፕ ለመጠጋት የጠየቁ በርካታ ተፈናቃዮችን ካምፖቹ ጠባብ በመሆናቸው መጨመር እንዳልተቻለ፣ ተጨማሪ ካምፕ ለመሥራት መታቀዱም ተመላክቷል፡፡

በምግብ እጥረት ምክንያት ዕቃቸውን እየሸጡ እየተሰደዱ መሆናቸውንና በምግብ እጥረት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች እንዳሉ ተፈናቃዮች ለሪፖርተር ቢናገሩም፣ አቶ ደረጀ ጉዳዩን በተመለከተ ምላሽ ሲሰጡ፣ “የምግብ እጥረት ቢከሰትም የተሰደደ ተፈናቃይ የለም፣ የሞተ ሰውም የለም” ብለዋል፡፡  አቶ አበባው በበኩላቸው  “የምግብ እጥረት የለም” ሲሉ ማስተባበላቸው በዘገባው ተመላክቷል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.