ዜና፡ በአዲስ አበባ በሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የሚካሄደው የዘፈቀደ እስር እና እንግልት እንዲቆም ኢሰመኮ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ የሚገኙ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በተለይም ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የዘፈቀደ እስር እና እንግልት እንደሚካሄድ መመልከቱን አስያውቋል። ተግባሩም በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል ሲል ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የማስረጃ ሰነድ የላችሁም በሚል ምክንያት በፖሊስ የተያዙ፣ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለእስር የተዳረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተለይ በኤርትራዊያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖራቸውን ተመልክቻለሁ ያለው ኢሰመኮ ከነዚህም መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ፣ ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን እና በተለያየ ጊዜ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በአብዛኛው የተለቀቁ መኖራቸውንም አስታውቋል።

የእስሩ ሰለባ የሆኑ በርካታ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች በመገኘት ኮሚሽኑ ክትትል ማድረጉን የጠቆመው መግለጫው ግለሰቦቹ ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ10 ቀናት በላይ በእስር ላይ መቆየታቸውን፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያትም “ስደተኛ መሆናችሁን የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ የላችሁም”፣ “ከካምፕ ለመውጣት ፈቃድ ሳይኖራችሁ ከተማ ውስጥ ተገኝታችኋል”፣ “የሥራ ፈቃድ ሳይኖራችሁ በሥራ ላይ ተሰማርታችኋል’’ በሚል መሆኑን መረዳቱን አመላክቷል።

በተጨማሪም ስደተኝነታቸውን የሚያሳይ ያልታደሰ መታወቂያ እያላቸው በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች መኖራቸውን፣ በአብዛኛው ደግሞ ጉዳያቸው እየተጣራ ስደተኛ ለመሆናቸው የሰነድ ማስረጃ ያላቸው እየተለቀቁ መሆኑን፣ የተወሰኑት ደግሞ ጉዳያቸውን በአግባቡ ለማስረዳት የቋንቋ ችግር እንደገጠማቸው ጭምር ኮሚሽኑ ለመገንዘብ መቻሉን በመግለጫው አካቷል።

የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች የመታወቂያ እድሳት ወይም የመታወቂያ አገልግሎት ላለፉት ሁለት ዓመታት በመቋረጡ ምክንያት ሊሰጣቸው እንዳለተቻለ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መረዳቱን ኮሚሽን በመግለጫው አስታውቋል።

የተቋረጠበትም ዋነኛ መንስኤዎችም አሠራሩን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ ታልሞ በጊዜያዊነት የተቋረጠና አዲሱ የምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊነቱ በታሰበው ፍጥነት ያልተቀላጠፈ በመሆኑ ነው የሚል ምክንያት እንደተሰጠው አስታውቋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ምዝገባ እና መታወቂያ እድሳት በአፋጣኝ ተመልሶ እንዲጀመር ማስቻል ነው ማለታቸውንም መግለጫው አካቷል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉም በመደበኛው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ደንቦች መሠረት በተገቢው ጥንቃቄ ልየታ በማድረግ በሕግ አግባብ ብቻ የሚፈጸም ሊሆን እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም አስታውቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.