ዜና፡ በትግራይ ክልል ለተከሰተው ርሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድሀኒት እጥረት  አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ሲል ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ለተከሰተው ርሀብ፣ ከፍተኛ የምግብና የመድሀኒት እጥረት  አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ሲል ጥሪ አቅርቧል። በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ሁለቱ ተደራዳሪዎች የፈረሙትን ግዴታዎች እንዲወጡ ሲል ያሳሰበው ኢሰመጉ ወደ ትግራይ ክልል የሚገቡ ሰብዓዊ እርዳታዎች ምግብን እና መድሀኒትን ጨምሮ በተገቢው መንገድ ለተጎጀዎች እንዲደርስ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ስርቆቶችን እና ህገ-ወጥ ንግዶችን እንዲቆጣጠር እና በእዚህም የፌደራል መንግስቱ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ሲል ጠይቋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲሁም የፌደራል መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች ስርቆት ፈጻሚዎች ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በህግ እንዲጠይቁ እንዲያደርጉ ብሏል።

በትግራይ ክልል ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ካስከተለው ጉዳት በላይ የከፋ ጉዳትን እንዳያደርስ እና ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጣ የፌደራል መንግስት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቀናጅተው እንዲሰሩ አሳስቧል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ እና የዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ያቋረጡትን የምግብ እና የመድሀኒት ድጋፍ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያስጀምሩ ጥሪ አቅርቧል። የሀገር ውስጥ ለጋሽ ተቋማት በትግራይ ክልል ያለው ከፍተኛ የምግብና መድሀኒት እጥረት እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛና አጣዳፊ መሆኑን በመረዳት አቅም በፈቀደ መጠን እርዳታዎችን በፍጥነት እንዲያቀርቡ እና የፌደራሉም መንግስት ይህንን እንዲያመቻችም ጠይቋል።

በመጨረሻም ኢሰመጉ በትግራይ ክልል ውስጥ የተፈጸሙ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የክትትልና የምርመራ ስራ ለመስረት እንዲሁም ቀድሞ የነበረውን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ዳግም ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.