ዜና፡ ሲኖዶሱ የግጭት ተሳታፊዎች ካለፈው ጦርነት በመማር ችግርን “በጥበብና በማስተዋል፣ በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ” ተወያይተው  እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28 ቀን 2015 .:­- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል እየተደረጉ ባሉ ግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ካለፈው የጦርነት ውጤት በመማር የተፈጠረውን ችግር “በጥበብና በማስተዋል እንዲሁም በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ” ተወያይተው እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ይህን ጥሪ ያቀረበው ትላንት ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ወቅታዊ ሀገራዊ ሰላምን በተመለከተ ከተወያየ በኋላ በሰጠው መግለጫ ነው፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም እጦትና የእርስ በርስ ግጭት ወደፊት ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለአገራዊ ሰላም የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ሲልም ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል።

ሲኖዶሱ “በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ ባለው የሰላም መደፍረስና የእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት የበርካታ ወገኖቻችን ውድ ሕይወት እያለፈ እና በርካታ የሀገርና የሕዝብ ሀብትና ንብረት እየወደመ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን ጥልቅ ሐዘን ተሰምቷታል” ብሏል።

በተጨማሪም ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ፍጡራን መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ያስረጋው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ በሀገራችን በኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ልንማጸን ይገባል ብሏል፡፡

ሲኖዶሱ በመግለጫው “በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት፣ የበርካታ ወገኖቻችንን ሕይወት የቀጠፈ ከመሆኑም በላይ ከሞት የተረፉት ወገኖቻችንም ለስደትና ለረሀብ የዳረገ፣ ለአካልና ለአእምሮ ስብራት ያጋለጠ ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ አድባራትና ገዳማትን እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትን ያፈረሰ እና መተኪያ የሌላቸውን ውድ ቅርሶቻችንን ያወደመ እጅግ በጣም አስከፊ ተግባር መሆኑ አይዘነጋም” ሲል  አስታውሷል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.