ዜና፡ ለሱዳን ቀውስ እልባት ለማስገኘት በአዲስ አበባ የኢጋድ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል፤ ኤርትራ እንደማትሳተፍ ተገልጿል፤ ተመሳሳይ ጉባኤ ካይሮ በተናጠል አዘጋጅታለች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3/2015 ዓ.ም፡- በሱዳን የተከሰተውን ቀውስ በዲፕሎማሲ ለመፍታት በአዲስ አበባ የኢጋድ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በሰኔ ወር መጀመሪያ ቀናት በጂቡቲ  በተካሄደው የኢጋድ መደበኛ የመሪዎች ጉባዔ ላይ ኢጋድ የሱዳንን ግጭት እንዲያሸማግሉ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን መሪዎች መሰየሙን ተከትሎ የሀገራቱ መሪዎች በአዲስ አበባ በመምከር ላይ ይገኛሉ።

ጉባኤውን እየመሩት ያሉት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሲሆኑ የሱዳን ሀይሎች የኬንያን መሪነት አንቀበለውም ማለታቸው ይታወሳል። በኢጋድ ከተሰየሙት አሸማጋዮች በተጨማሪ የአሜሪካን መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ ሞሊ ፊም በጉባኤው ላይ መገኘታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት አስታውቋል።

በጉባኤው ላይ ኤርትራ እንደማትሳተፍ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ገልጸውልኛል ሲሉ የሱዳን ላዕለዋይ ምክር ቤት ምክትል ማሊክ አጋር መናገራቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ድረገጽ ዘግቧል። የሱዳንን ግጭት ለመፍታት በአለም አቀፍም ይሁን በቀጠናው ሀገራት በኩል የሚቀርቡ ጥረቶች የፖለቲካ ባዛሮች በመሆናቸው ኤርትራ በባዛሩ የመሳተፍ ፍላጎት የላተም ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ነግረውኛል ሲሊ ማሊክ አጋር መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል። የሱዳን ጉዳይ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት ሁኔታዎቹን እንዳያባብሰው ስጋት እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱ መግለጻቸውን ዘገባው አካቷል።

በሌላ ዜና በሳምንቱ አጋማሽ ተመሳሳይ ጉባኤ ካይሮ በተናጠል ማዘጋጀቷን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የሊቢያ፣ ቻድ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች እንዲገኙ መጋበዛቸውን ዘገባዎቹ አመላክተዋል። የሱዳን ግጭት በአጎራባች ሀገራቱ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖም እንደሚመከርበት ዘገባዎቹ ጠቁመዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.