ቃለ መጠይቅ፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለመመስረት በትግራይ በኩል ያለው ሂደት ተገባዷል፤ ቀሪው ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ ነው: ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም- የኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25/ 2015 ዓ.ም፡– የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም ጫፍ ላይ ቢደረስም የግዜያዊዉ መንግስት አመሰራረቱ ከፍተኛ ውዝግብ እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ እና ውናት ሂደቱ ዲሞክራሲያዊ ባለመሆኑ ከወዲሁ ውጤቱ እንዲታወቅ አድርጎታል ሲሉ በመተቸት እንደማይሳተፉ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል። በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የተቃውሞ ድምጹ ያልተሰማው ሊቀመንበሩ ላለፉት ሁለት ዓመታት በእስር ላይ የሚገኘው አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ብቻ ነው።

በትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ አነሳሽነት የጊዜያዊ መንግስት ለመመስረት ያስችላል ዘንድ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል። ኮሚቴው የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቶ የካቲት 22 እና 23 በመቐለ 400 የክልሉ ተወካዮች የተሳተፉበት ኮንፈረንስ አካሂዷል።

የጊዜያዊ መንግስት ለማዋቀር የተቋቋመው ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር ቆይታ አድረገዋል፡፡ ምክትል ሊቀመንበሩ የጊዜያዊ መንግስት የማቋቋሙ ሂደት በትግራይ በኩል መገባደዱን ጠቅሰው ቀጣዩ ስራ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚደረግ ድርድር መሆኑን አመላክተዋል።

ስለሂደቱ ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት ሁሉን ያካተተ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ጠቁመው የተፎካካሪ ፓርቲዎች በኮንፈረንሱ ላይ አለመገኘት ለእነሱ አሳዛኝ እና አለመታደል ነው፤ ለወደፊት እንቅስቃሴያቸው ይጠቅማቸው ነበር ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

“ሌላ ያሰሉት ነገር ካለ እንጃ” ሲሉ የገለጹት መምህር ሙሉወርቅ ለትግራይ ግን ብዝሃነት እንዲሰፍን እና እንዲለመድ አንድ እድል ይመስለኛል ብለዋል። የነሱም ሆነ አሁን በመቋቋም ላይ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ለትግራይ ትልቅ እድል መሆኑን አመላክተው ተረዳድተህ ተግባብተህ መሄድ እንጂ መንግስት አፍርሰህ እንደ አዲስ እኩል ሁነን እንጀምር ማለት እንደ አሰራር የሚያስኬድ አይመስለኝም ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲዎቹን ውሳኔ ተችተዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በኮንፈረንሱ ላይ ቢሳተፉ ሀሳባቸውን ለመሸጥ እድሉን ያገኙ ነበር ብለዋል።

የትግራይ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ኮሚቴውን እንደማይቀበሉት መግለጻቸውን ተከትሎ የኮሚቴውን ቅቡልነት በተመለከተ የጠየቅናቸው መምህር ሙሉወርቅ በመጀመሪያ ኮሚቴውን ያዋቀረው መንግስት መሆኑን ተቁመው ቅቡልነት የሚለው ጉዳይ በሁለቱ አካላት መካከል ውል ከነበረ እና እነሱ እንዲሳተፉ የሚያዝ ቀመር ከነበረ ትክክል ይሆናል፤ ነገር ግን እንደዚያ አይነት ስምምነት የነበረ አይመስለኝም ብለዋል። ጉዳዩን ሲያብራሩም ብዙዎቹ እንደተረዱት የፕሪቶርያው ስምምነት በፌደራል ምንግስትን በሚመራው ብልጽግና እና በህወሓት መካከል የተካሄደ ነው ያሉት መምህር ሙሉወርቅ ይህም ማለት ህወሓት በስምምነቱ መሰረት የራሱን እያደረገ ነው፤ በራሱ በሚያደርገው ነገር ላይ በዚህ አይነት አካሄድ መሄድ አለበት ብሎ አስቦታል፤ ነገር ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የህወሓትን አካሄድ አንቀበልም ማለታቸው ነው ብለዋል።

በተጨማሪም አንደኛው የሚያቀርቡት ምክንያት መንግስት የለም የሚልም ይገኝበታል ሲሉ ገልጸው መንግስት የለም ካሉ መንግስት የሚለውንም አይቀበሉም ማለት መሆኑን ጠቁመው ታዲያ ማንን ነው እንዲያስተካክል የሚጠይቁት ሲሉ ተችተዋል።

የፓርቲዎቹ ጥያቄያቸው እኛ ላይ ሳይሆን መንግስትን ነው ያሉት ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም እኛማ እንደሚታወቀው በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ተጠርተን ነው የተካተትነው፤ የትግራይ ሙሁራን የመረጧቸው ናቸው አላሉም፤ ሶስት ከሙሁራን ወሰድን አሉ እንጂ ሲሉ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ባለመሳተፋቸው በጊዜያዊ መንግስቱ አይካተቱም ማለት ነው ብለን የጠየቅናቸውን ጥያቄም ሲመልሱ ጊዜያዊ መንግስቱ አካታች እንዲሆን በሚል ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በኮንፈረንሱ ላይ ባይሳተፉም በሚመሰረተው መንግስት ላይ ግን ጉባኤው ኮታ ሰጥቷቸዋል ሲሉ ገልጸዋል። ሂደቱን አይተው ውሳኔያቸውን ያስተካክሉ ይሆን በሚል ዝግ አላደረግነውም ያሉት ሙሉወርቅ መንግስት ስለሆነ የሚመሰረተው ሊመጡ ይችላሉ ብለን አሁንም ክፍት አድርገነዋል ብለዋል። ነገር ግን ለመንግስት ምስረታው የማይደርሱ ወይንም የማይሳተፉ ከሆነ ግን በአማራጭነት የነሱ ኮታ ለሙሁራን እና ለሰራዊቱ ኮታዎች እኩል እንዲካፈሉት እና እንዲጨመር አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል። ፓርቲዎቹ የማይሳተፉ ከሆነ በሚል ጉባኤው ኮታውን ህወሓት እንዳይጠቀምበት መወሰኑን ነግረውናል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ መቼ ይቋቋማል? ምን ቀረ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ እኛ ጨርሰናል ማን ምን ቦታ ይውሰድ በሚለው ዙሪያ ለጉባኤው አቅርበን ጉባኤው ይሄ ይጨመር ይሄ ይቀነስ የሚል ጨምሮበት ተነጋግሮ ቀመሩን አስቀምጠን ተወስኖ አልቋል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የቀረው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ነው፣ እሱም አቅጣጫ ተቀምጦለታል ብለዋል። ዋናው ቀጣይ ስራ በግዜያዊ መንግስቱ የሚካፈሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ተሳታፊ ድርጅቶቹ መሆኑን የጠቀሙት መምህር ሙሉወርቅ ይህም ማለት የየራሳቸውን ተወካዮች ዝርዝር ይዘው በመምጣት ቁጭ ብለው በቀመሩ መሰረት ስልጣኑን መከፋፈል ነው ብለዋል።

ጉዳዩን በዝርዝረ ሲያስረዱም ለምሳሌ ህወሓት ይህን ያክል በመቶ ይይዛል፣ በዚህም ይህን ይህን ቦታ ያገኛል ብለን አስቀምጠናል፤ በመሆኑም የራሱን ተወካዮች ዝርዝር ይዞ ይመጣል። ከሰራዊቱም የተመረጡት ዝርዝር ይቀርባል ሌሎቹም እንዲሁ፣ ከዚያም ሁሉን አቀናጅቶ መመስረት ነው ብለዋል።

የግዜያዊ አስተዳደሩን ሊቀመንበር ጨምሮ ቦታዎቹ ላይ ማን ምን እንደሚይዝ መቀመጡን ገልጸው ስለሆነም ሁሉም ነገር የታወቀ ይመስለኛል፤ በኛ በኩል ያለውን ስራ ጨርሰናል ብለዋል።

በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት የማእከላዊ መንግስቱም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ቦታ ስለሚኖረው በኮንፈረንሱ ውሳኔ ላይ ቢያንስ በመጀመሪያ ሊስማማ ይገባል ያሉት መምህር ሙሉወርቅ እራሳችሁ አቋቁሙ ተቀብየዋለሁ የሚል ከሆነ ሂደቱ ያበቃል፤ አልተቀበልኩትም ካለ ግን ወደ ድርድር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።አስ        

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.