ዜና፡ ስልሳ አምስት አመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ማደጉ ተገለጸ

ፎቶ- የኢትዮጵያ አየር መንገድ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉሩፕ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አቪየሽን አካዳሚ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ማደጉ ተገለጸ።

አካዳሚው ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ በማደጉም በቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ፕሮግራም በኤሮስፔስ እና መስተንግዶ ዘርፎች ስልጠና መስጠት መጀመሩን እንዲሁም በመጀመሪያ ድግሪ በአውሮፕላን ጥገና፣ በኤሮኖቲካል ኢንጂነሪንግ፣ በአቪየሽን አስተዳደር፣ በቱሪዝም እና መስተንግዶ መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ባወጣው መግለጫ  ጠቁሟል።

ስልሳ አምስት አመታትን ያስቆጠረው አካዳሚ ከብዙ ጥረት እና ኢንቨስትመንት በኋላ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ማሳደጋችን የአየር መንገዱን የዘመናት እድገት ጥረት እና እድገት ስኬት ነው ሲሉ የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል። በአየር ኢንደስትሪው ያለንን ቀዳሚ ሚና እናስቀጥላለን ያሉት ስራ አስፈጻሚው ዩኒቨርስቲው በቅድመ ምረቃ እና ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞቹ የሰለጠነ የአቪየሽን ኢንደስትሪ የሰው ሀይል በማፍራቱ ረገድ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። ዩኒቨርስቲው ለኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕም ሆነ በቀጠናው ለሚገኙ አየር መንገዶች የሰለጠና የሰው ሀይል ባለሞያዎችን ማፍራት እንደሚጠበቅበትም አመላክተዋል።

የዩኒቨርስቲው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካሴ ይማም በበኩላቸው የአየር መንገዱ የስኬት ሚስጥር የሆነው የስልሳ አምስት አመቱ አካዳሚያችን ወደ ዩኒቨርስቲ ማደጉን ስናበስር ደስተኞች ነን ሲሉ ገልጸው በዲግሪ ደረጃ ከሀገር ውስጥ እና ከሌሎች ሀገራት ተማሪዎችን እንደሚቀበል ጠቁመዋል። ዩኒቨርስቲው በፍጥነት በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያንም ሆነ የአህጉሩን የአቪየሽን ሴክተር መደገፉን እንደሚቀጥል አመላክተዋል። የአቪየሽን አካዳሚው ከወራት በፊት በሃዋሳ የስልጠና ማዕከል መክፈቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በድረገጹ ይፋ ያደረገው መግለጫ አካቷል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.