ጥበብ እና ባህል: 83ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል በእንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው

በመካሄድ ላይ ያለው የአገው ፈረሰኞች ፌስቲቫል ከፊል እይታ። ፎቶ፡ አዊ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ

አዲስ አበባ፣ጥር 22/ 2015 ዓ.ም፡– 83ኛው የአገው ፈረሰኞች ማህበር የምስረታ በዓል በአማራ ክልል በምትገኘው አዊ ዞን፣ እንጅባራ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ነው።፡፡

ከአዊ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በዓሉ “አምራች ፤ ዘማች የአገው ፈረሰኞች ማህበር “በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

የአገው ፈረሰኞች ማኅበር የአገው አባቶች ከሌሎች አባት አርበኞች ጋር በመተባበር የጣልያንን ወራሪ ጦር ዓድዋ ላይ ድል መቀዳጀታቸውን ለመዘከር በየዓመቱ ጥር 23 በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚከበር በዓል ነው፡፡

ማኅበሩ በ1932 ዓ.ም ከ30 በማይበልጡ አባላት የተመሰረተ ሲሆን÷ በአሁኑ ወቅት ከ 62 ሺ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን የአባላቱን ቁጥር 150 ሺ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው።

ሰሞኑን የአገው ፈረሰኞች በዓል የአዊ ብሄረሰብ መለያ የሆነውን የአገው ፈረሰኞች በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ድርጅት (UNESCO) በማስመዝገብ የሃገራችን አንዱ ልዩ ገጽታ ማሳያ ለማድረግ እየተሠራ ነው በማለት የአማራ ክልል መንግስት መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.