ዜና፡ የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞቻቸዉ ያለፈቃድ በስራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቅሶ 15 የዉጭ መገናኛ ብዙሃንን አገደ

አዲስ አበባ፣ጥር 22/ 2015 ዓ.ም፡– የሶማሊ ክልል የኮሙዩኒኬሸን ቢሮ በክልሉ ይንቀሳቀሱ የነበሩ 15 የውጭ ሚዲያዎችን ማገዱ ተገለጸ። መቀመጫቸውን በክልሉ ያደረጉ ቢቢሲ እና የአሜሪካ ድምጽ የሶማሊኛ ቋንቋ ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የ15 የዉጭ መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ያለ ህጋዊ ፈቃድ መንቀሳቀሳቸውን ኮንኗል። የመገናኛ ብዙሃኑ የክልሉ ወኪሎች ህጋዊ ማረጋገጫና ፈቃድ ሳይዙ ይንቀሳቀሱ ነበር ሲሉ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ባለስልጣን ለአዲስ እስታንዳርድ አስታውቀዋል።

በጥር 19 2015 ዓም ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተጻፈ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ የሚገኙ ፈቃድ ሳይኖራቸው ለውጭ ሚዲያዎች የሚሰሩ ግለሰቦች ላይ ከህግ አካላት ጋር በመተባበር እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

በደብዳቤው እንደተገለጸው በክልሉ ከባለስልጣኑ ምንም አይነት ህጋዊ ፈቃድ ሳይወስዱ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሚዲያዎች ተወካዮች እና ጋዜጠኞች መኖራቸውን በምርመራ ደርሸበታለሁ ብሏል። በደብዳቤው ላይ ያለህጋዊ ፈቃድ ተንቀሳቅሰዋል የተባሉት ሚዲያዎች ግን በስም አልተዘረዘሩም።

ከባለስልጣኑ የተላከውን ደብዳቤ ተከትሎ ጥር 20 2015 ዓም የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የ15 የውጭ ሚዲያዎች ስራቸው እንዲቋረጥ አዟል። በክልሉ ቢሮ እንቅስቃሴያቸው እና ስርጭታቸው እንዲቋረጥ ከተደረጉት የውጭ ሚዲያዎች መካከል BBC Somali, MM TV, Universal TV, Horyaal TV, RTN TV, Universal TV, Five TV, Sahan TV, Horn Cable TV, and Goobjoog TV ይገኙበታል።

ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የተላከውን ደብዳቤ በማጣቀስ የክልሉ ቢሮ እገዳውን ቢጥልም ለእገዳው ዋናውን ሚና የተጫወተው የክልሉ ቢሮ ነው ሲሉ የገለጹት የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አብዱልራዛቅ ሀሰን ያልታደሰ ፈቃድ የሚለው ጉዳይ ማታለያ ነው ሲሉ ተችለዋል።

ያልታደሰ ፈቃድ ብቻውን ለእግዱ ምክንያት አይደለም ሲሉ ለአዲስ እስታንዳርድ የገለጹት ሊቀመንበሩ ሚዲያዎቹ በክልሉ ገዢ ፓርቲ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎችን፣ በክልሉ ያሉ ግጭቶችን እና ድርቅ የሚያጋልጡ ዘገባዎችን በመስራታቸው ነው ብለዋል።

በየስድስት ወሩ የሚታደሰውን ፈቃድ እንዲታደስላቸው የክልሉን የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሲጠይቁ እንደነበር ያስታወቁት ማህበሩ ሊቀመንበር አብዱልራዛቅ ሀሰን የቢሮው የእግድ ውሳኔ በአጋባቡ የሚተቹ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሚዲያዎችን ለማፈን የሚደረግ ጥረት ነው ሲሉ ኮንነዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ባለስልጣን በሶማሌ ክልል ፍቃድ ሳይኖራቸው ስለሚንቀሳቀሱ የውጭ ሚዲያዎች ጉዳይን በተመለከተ ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ጋር የውስጥ ማስታወሻ መለዋወጡን ለአዲስ እስታንዳርድ ያረጋገጠ ሲሆን ስለእገዳው ግን ምንም የምናውቀው ነገር የለም ብሏል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.