ጥልቅ ትንታኔ፡ ለወራት በዘለቀው ግጭት ከምዕራብ ኦሮሚያ የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ማህበረሰብ አባላት በአዲስ አበባ እና በአርሲ ዞን ተጠልለው ይገኛሉ

በአዲስ አበባ የአማራ ማህበረሰብ አባላት ከላይኛው ጫፍ ከግራ ወደ ቀኝ፡ ሴቶች፤ አረጋውያን እና ህፃናት: ታምሩ ደገፋ ሰው ተፈናዋዮችን ሲያፅናኑ፤ ካሳየው ለማ እና ቢራራ ጌታነው

በ እቴነሽ አበራ @EteneshAB እና ጌታሁን ፀጋዬ @GetahunTsegay12

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14፤2014-በምዕራብ ኦሮሚያ ይኖሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ማህበረሰብ አባላት ለወራት በዘለቀው ጥቃትና እንግልት ምክያት ተፈናቅለው በአዲስ አበባ መጠለያ አየፈለጉ ነው። ሌሎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን እንዲሄዱ መደረጉን አዲስ ስታንዳርድ ባደረገችው ምርመራ አረጋግጣለች።

ከጥር ወር መጨረሻ ሳምንት ጀምሮ የተፈናቀሉ የአማራ ማህበረሰብ አባላት በመዲናይቱ አዲስ አበባ በሚገኙ ሁለት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መጠለያ ፍለጋ ላይ እንደነበሩ አዲስ ስታንዳርድ ሪፖርት ደርሷታል። በወቅቱ ከሆሮ ጉድሩ ዞን የተፈናቀሉት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ መስቀል አደባባይ አቅራቢያ በሚገኘው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የነበረ ሲሆን ከምእራብ ወለጋ የተፈናቀሉት ደግሞ በየካ ክፍለ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበሩ። አዲስ ስታንዳርድ ሁለቱንም ቦታዎች ጎብኘታ ተፈናቃዮችን እና የማህበረሰብ አስተባባሪዎችን አነጋግራለች።

ከሆሮ ጉድሩ ዞን ተፈናቅለው በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ
በጥር ወር መጨረሻ ሳምንት 30 ህፃናትን ጨምሮ በድምሩ 107 ተፈናቃዮች በአዲስ አበባ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን መግባታቸውን ዶይቸ ቬለ አማርኛ ዘግቧል። በመዲናይቱ ከደረሱት ተፈናቃዮች መካከል አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንደማያውቁ በዘገባው ተጠቁሟል። ተፈናቃዮቹ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሃይማኖት ተቋማት እና በነዋሪዎች ላይ በጅምላ ጥቃት ሲያደርሱ እንደነበር ተናግረዋል። ተፈናቃዮቹ ለአካባቢው አስተዳደር ያቀረቡት ተደጋጋሚ አቤቱታ ሰሚ ባለማግኘቱ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰው ጥቃቱ ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ መጀመሩን እና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት በነሀሴ ወር ቢሰማሩም ጥቃቱን መከላከል እንዳለቻሉ ተናግሯል። “የመንግስት ሃይሎች ጭፍጨፋ ሲደርስባቸው ስናይ ከዚህ በላይ መቆየት አልቻልንም” ብለዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ተፈናቃዮቹ ለ3 ቀናት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንደቆዩ የተገነዘበች ሲሆን ወደ ዋና ከተማዋ የመጡበት ምክንያት ደገሞ “የኦሮሚያ ክልል መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅ” ነበር። አዲስ ስታንዳርድ ቤተክርስቲያኑን በጎበኘችበት ወቅት ተፈናቃዮቹ በፖሊስና በከተማው አስተዳደር ባለስልጣናት ታጅበው በአውቶብስ ሲጫኑ ተመልክታለች። በወቅቱ ተፈናቃዮቹ ለሚዲያ መናገር በጣም ይፈሩ ነበር። ፖሊሶች ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያመጡላቸውን እርዳታ እንዳይሰጧቸው እና እንዳያናግሯቸው ክልከላ ሲያደርጉ እንደነበር ታይተዋል። አዲስ ስታንዳርድን ካናገረቻቸው ተፈናቃዮች መካከል አንዱ “ወደ መጣንበት እየተመለስን ነው” ብሏል።

“ቋሚ መኖሪያ ቀያችን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዱንጉሩ ወረዳ ሆማ ጋሌሳ እና ቄሩ ቀበሌዎች ነበር። በግንቦት ወር የደረሰብንን የኦነግ/ሸኔን ጥቃት ሸሸን። በጥቃቱ የተነሳ በርካቶች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል ቤቶች እና ቤተክርስትያናተን ጨምሮ በሚሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶች ወድመዋል።”

አቶ ደስታ

የተፈናቃዮቹ ‘ወኪል’ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደስታ፣ ተፈናቃዮች በአውቶብስ ከእስቲፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከተወሰዱ ከቀናት በኋላ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከሁለት ሳምንት በፊት ከአርሲ ዞን 107 ተፈናቃዮች አዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ስጋት ለመናገር መምጣታቸውን አስታውሰው፤ እስከ ግንቦት 2013 ዓም ድረስ በዚያው ዞን ሲኖሩ እንደነበር ገልጸዋል።

“ቋሚ መኖሪያ ቀያችን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዱንጉሩ ወረዳ ሆማ ጋሌሳ እና ቄሩ ቀበሌዎች ነበር። በግንቦት ወር የደረሰብንን የኦነግ/ሸኔን ጥቃት ሸሸን። በጥቃቱ የተነሳ በርካቶች ተገድለዋል፤ ቆስለዋል ቤቶች እና ቤተክርስትያናተን ጨምሮ በሚሊዮን ብር የሚገመቱ ንብረቶች ወድመዋል። በዚህም የተነሳ ወደ አርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ጎሎጎታ ቀበሌ በሚገኘው መድሀኒአለም ቤተክርስትያን ተሰደድን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መጠለያ እየፈለግን ነው ” በማለት አብራርተዋል።

አቶ ደስታ በአሁኑ ሰዓት በአርሲ ዞን 419 ተፈናቃዮች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። ደስታ አያይዘውም ከአርሲ ዞን ምንም አይነት እርዳታ ስላላገኘን ስጋታችንን ለመግለፅ ወደ አዲስ አበባ መጥተናል ሲሉ ተደምጠዋል። ‘’እኛ ጥረት ብናደርግም፣ ሁሉም የመንግሥት አካላት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ጉዳያችንን ከቁብ ሳይቆጥሩት ችላ ብለውታል’’ ሲሉ አቶ ደስታ ተናግረዋል ።

እንደ አቶ ደስታ ገለጻ፣ የጸጥታ አካላት እና የእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ኮሚቴ ለተፈናቃዮቹ እንደተናገሩት በቤተክርስቲያኑ ውስጥ መገኘታቸው ከ35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የጸጥታ ክትትል እንደሚጠይቅ እና ‘የሚበጀው’ አማራጭ ወደ አርሲ መመለስ መሆኑን እንደነገሯቸው አስረድተዋል። አቶ ደስታ የእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በቆዩባቸው ሁለት ሳምንታት የምግብና አስፈላጊ መገልገያዎችን ሲያቀርቡላቸው እንደነበር ገልጸዋል። የአባቶቻቸውን ስም ባያስታውሱም አቶ ዘላለም እና ታዬ የተባሉ ተፈናቃዮቹን ለትራንስፖርት እና ለአንዳንድ ተያያዥ ወጪዎች ሲረዱ እንደነበር ደስታ አብራርተዋል። እንደ አቶ ደስታ ገለጻ፣ መምህር ዘላለም 22,200 ብር የሰጧቸው በጎ አድራጊ ግለሰብ ነበሩ። አያይዘውም አቶ ታዬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የጸጥታ ሃይል ሃላፊ መሆናቸውን አስረድተው ለተፈናቃዮቹ ሁለት የህዝብ አውቶብሶችን አቅርበው እንድነበር ተናግረዋል። አዲስ ስታንዳርድ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የጸጥታ ሃይሎችን ለተጨማሪ ማብራሪያ ለማናገር ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።

ታምሩ ደገፋ ሰው ተፈናቃዮችን ሲያፅናኑ

አዲስ ስታንዳርድ ካነጋገረቻቸው ተፈናቃዮች አንዱ እያሱ ሙሉጌታ ነው። ላለፉት 9 ወራት የኦርሚያ ክልል መንግስትም ሆነ ሌሎች የመንግስት አካላት እንዳልረዷቸው ተናግረዋል። “የጎሎጎታ መድሀኒአለም ቤተክርስትያን እና የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ በማቅረብ ከፍተኛ እገዛ አድርገዋል” ብለዋል። አቶ ደስታ እና እያሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው) ኢላማ ያደረጋቸው በብሄር ማንነታቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኦሮሚያ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በመርቲ ወረዳ በነበራቸው በ9 ወራት ቆይታ ለ419 ተፈናቃዮች 30 ኩንታል ስንዴ ብቻ የረዳቸው መሆኑን አቶ ደስታ ገልጸው “በጣም ጥቂቶቻችን የቀን ሥራ በመስራት ገቢ ማግኘት የቻልን ቤት ተከራይተን ስንኖር አብዛኞቻችን ግን መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብ፣ ልብስ እና ጥበቃ እያደረጉልን የገኛሉ። ከ30 ኩንታል ስንዴ በስተቀር የመንግስት አካላት ምንም አይነት እገዛ አላደረጉልንም” ሲሉ አቶ ደስታ ዘርዝረዋል።

የመርቲ ወረዳ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ረታ ሀይሉ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት የተፈናቃዮች ቁጥር 80 ነው።”የመርቲ ወረዳ ኃላፊዎች የአካባቢውን ነዋሪዎችና የሚመለከታቸው አካላትን በማስተባበር ለ80ዎቹ ተፈናቃዮች ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ አቅርበዋል” ብለዋል። አዲስ ስታንዳርድ የደረሳት የተፈናቃዮች ቁጥር 80 ሳይሆን 419 እንደሆነ ላቀረበችው ጥያቄ፣ አቶ ረታ፣ በቅርቡ ቦታውን እንደተረከቡና የቀድሞው ሪፖርት የሚያመለክተው 80 ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።”እኔና የወረዳው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ወደ ጎሎጎታ ቀበሌ ሄደን እንደምናያቸው እና እንደምንረዳቸው አረጋግጣለሁ” በማለት ቃል ገብተዋል።

ከምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በየካ ክፍለ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ

አቶ ቢራራ ጌታነው የተወለደው በደቡብ ጎንደር ታች ጋይንት ወረዳ ሲሆን ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ ወለጋ በሱቡ ስሬ ወረዳ በቆጂማ ቀበሌ ነዋሪ ነው። በበቆጂማ ቀበሌ ህይወቱን “ተስማሚ” እንደነበር ያስታውሳል። ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ባለፈው አመት መጀመራቸውን አብራርተዋል። “አብዛኞቹ ዘመዶቻችን ተገድለዋል፣ ንብረቶቻችን ወድሟል” በማለት ተናግረዋል። ጥቃቱ በጥቅምት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ መጀመሩን ቢራራ አስረድተዋል። “ኦነሰ/ሸኔ ስልሳ ዘጠኝ ሰዎችን የገደለ ሲሆን በርካቶች ወደተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለዋል። የተወሰነው ጥቅምት 12 ቀን ወደ አዲስ አበባ መጥተን እዚህ የካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውጪ ተጠልለናል” ብለዋል።

በወቅቱ አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረቻቸው አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ስለ መፈናቀላቸው ሁኔታ ላቀረበችላቸው ጥያቄ ለደህንነታቸው ስጋት መሆኑን ጠቅሰው የመጡበትን የቀበሌና የወረዳ ስም ለመግለፅ ፈቃደኛ አልነበሩም። “ጥቃት እንዳይደርስብን እንፈራለን እና ወደ መጣንበት መመለስ አንፈልግም” ብለዋል። አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ማን እየረዳቸው እንደሆነ አዲስ ስታንዳርድ ቢራራን ጠይቃለች። “የካ ክፍለ ከተማ እና ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቢሮ እርዳታ ፈልገን ሄደን ነበር ነገር ግን ምላሽ አልሰጡንም። የየካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን እንዲሁም የአማራ ክልል መንግስት ምንም አይነት እርዳታ አላደረጉልንም። ይሁን እንጂ ግለሰቦችና አንዳንድ በጎ ፈቃደኞች ምግብና ልብስ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ድጋፍ አግኘተናል” ሲሉ አስረድቷል። አዲስ ስታንዳርድ ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችን እና ጨቅላ ሕፃናትን በስፍራው ተመልክታለች። ቁጥራቸውም 135 ሰዎች ሲሆኑ 35 አባወራዎች መሆናቸውን ቢራራ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የአማራ ማህበረሰብ አባላት ሴቶች፤ አረጋውያን እና ህፃናት

ራሱን ‘ወሰን የለሽ በጎ ፈቃደኛ’ መሆኑን የገለጸው አቶ ታምሩ ደገፋ ሰው፣ ከአዲስ አበባና ከውጪ ሃገር የመጡ በጎ ፈቃደኞችን እያስተባበረ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግሯል።
“እኔ ድንበር የለሽ በጎ ፈቃደኛ ስሆን ከአገር ውስጥ እና ከውጪ የሚመጣን እርዳታ ለተፈናቃዮቹ ምግብና ልብስ ለማቅረብ እያስተባበርኩ ነው። ላለፉት ጥቂት ቀናት ምግብ እና ልብስ አቅርበናል። አብዛኞቹ አማሮች ቢሆኑም ከነሱ መካከል የተወሰኑ ኦሮሞዎች አሉ” ብሏል።

አቶ ቢራራ የነበረውን ሁኔታ እያስታወሱ፣ “ምስራቅ ወለጋ እያለን ለክልሉ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና መሰል አካላት አሳውቀናቸው ሊረዱን መጥተው ነበር። ሰኔ 2013 ዓ.ም ሊረዱን ከተሰማሩት የኦሮሚያ የጸጥታ ሃይሎች መካከል አንድ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ሲገደል አንድ ፖሊስ ቆስሏል። ጥቃቱ በመባባሱ የተሰማራው ሃይል አካባቢውን ለቆ ስለነበር ለጥቃት ተጋለጥን። ጥቃቱን ያደረሱት ኦሮሞ ነዋሪዎች አይደሉም። ይልቁንም የታጠቀው የኦነሰ ቡድን ነው። እንዲያውም እኛን ከጥቃቱ ለመከላከል የሞከሩ እና በመጨረሻ ራሳቸው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ አንዳንድ ኦሮሞዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ይዘው ተፈናቅለው እዚህ አዲስ አበባ ገብተዋል” ሲል አስረድቷል።

እንደ ቢራራ ገለጻ ከሱቡ ስሬ 22 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ የተፈናቀሉ አማሮች ተፈናቅለዋል። “በወረዳው ውስጥ የመንግስት ተወካዮችም እና የወረዳ አመራሮች አካባቢውን ለቀው ቢሄዱም የክልሉ መንግስት ከአካባቢው ኦፊሴላዊ ግንኙነት ባለማግኘቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ ያውቅ ነበር” በማለት ግምቱን አስቀምጧል። ቢራራም አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሀሳብ እያቀረቡላቸው መሆኑን እንደስጋት አንስተዋል። “በአካባቢው እስካሁን የደህንነት ስጋት አለ። በአካባቢው የጸጥታ ችግር እንዳለ መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። ከባህር ዳር ወደ ነቀምት የሚወስደው መንገድ ከተዘጋ ከአንድ አመት በላይ ሆኖታል። ወደ ቤት አንመለስም። ንብረታችንና ቤቶቻችን ሙሉ በሙሉ አመድ ሆኗል። ብዙ ዘመዶቻችን ሞተዋል። አሁንም ብዙ ሰዎች እንየታፈኑ ይገኛሉ። ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እስኪመለሱ ድረስ እዚሁ አዲስ አበባ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን” ሲል አስረድቷል።

“ንብረታችንና ቤቶቻችን ሙሉ በሙሉ አመድ ሆኗል። ብዙ ዘመዶቻችን ሞተዋል። አሁንም ብዙ ሰዎች እንየታፈኑ ይገኛሉ። ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እስኪመለሱ ድረስ እዚሁ አዲስ አበባ ጊዜያዊ መጠለያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን”

ቢራራ

ልክ እንደ ቢራራ ሌላው ተፈናቃይ አቶ ካሳየው ለማ አማራና ኦሮሞ ተቻችለው ለዘመናት ሲኖሩ እንደነበር አስታውሰው “ኦሮሞዎች ወንድሞቻችን ናቸው እና ከእነሱ ጋር ችግር የለብንም” ብለዋል። አቶ ካሳየው ዝርዝር መረጃን መስጠት ባይችሉም በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል ‘አለመተማመን’ እንዲፈጠር ያደረጉት ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያሉት የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ናቸው” ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ስታንዳርድ ተፈናቃዮቹን እየጎበኙ ያሉትን የአማራ ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ያረጋል አሰፋን አነጋግራለች። ማህበሩ መሰረቱን አዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን በዋናነት በበጎ ፍቃድ ስራዎች ላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ”አልባሳት፣ ብርድ ልብስ እና ምግብ እየሰጠን ነው። የተፈናቃዮቹን ድምጽ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለማድረስ ነው እዚህ የተገኘነው” ብሏል። አቶ ያረጋል አያይዘውም የመንግስት ባለስልጣናት እና የየካ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ስለሁኔታው ግንዛቤ ቢኖራቸውም ለመርዳት ፍቃደኛ አልሆኑም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።”ምግብና ልብስ ለማቅረብ ፈቃደኛ ለሆኑ በጎ ፈቃደኞችን ጥሪ አቅርበናል። ተፈናቃዮቹ ከምግብና ልብስ ጋር በተያያዘ ብዙ ችግር አላጋጠማቸውም። ትልቁ ፈተና መጠለያ ነው። አንዳንድ በጎ ፈቃደኞች ድንኳን ቢሰጡም ድንኳኑን ለመትከል ክፍት ቦታ ማግኘት አልቻልንም። ቦታውን ከከተማው አስተዳደር እየጠየቅን ነው” ብለዋል። አዲስ ስታንዳርድ የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደርን ለማናገር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።

ባለፈው ታህሳስ ወር አዲስ ስታንዳርድ በምስራቅ ወለጋ ዞን የተፈጠረውን ግጭት ሸሽተው የወጡ የአማራ ማህበረሰብ አባላት በአዲስ አበባ ቤተክርስትያን ቅጥር ግቢ እና ወጣት ማእከላት በተዘጋጁ ጊዜያዊ ካምፖች መጠለላቸውን መዘገቧ ይታወሳል።

በተመሳሳይ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዘነበወርቅ አካባቢ የሚገኘው የአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ሓላፊ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደተናገሩት ከምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለዋል ስለተባሉት ተፈናቃዮች “የተፈናቀሉ 120 የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ተጠልለው የቆዩ ሲሆን በፌደራል መንግስት፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልላዊ መንግስታት እርዳታ ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን ሌሎች ቦታዎች እንዲዛወሩ ተደርጓል” ብለው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመጉ) ባወጣው ሪፖርት በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ነዋሪዎች ላይ የደረሰውን ግድያና መፈናቀል አጋልጧል። ዘገባው ነዋሪዎቹን ጠቅሶ እንደገለፀው በመንግስት ባለስልጣናት ሸኔ የተባለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል። የአማራ ማህበረሰብ አባላት በአፀፋው 60 ሰዎችን መግደላቸውንም ኮሚሽኑ አስታውቋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.