photo credit: ERIC LAFFORGUE
በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8/2015 ዓ.ም፡– በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከ2010 እስከ 2020 በተደረገ ጥናት የጥርስ ጤንነት አጠባበቅ ልማድ እጅግ አነስተኛ መሆኑ ተረጋግጧል። በኢትዮጵያ የጥርስ ጤንነት አጠባበቅ ልማድ ያላቸው ሰዎች አስራ ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ የሆኑ ዜጎቿ ብቻ ናቸው ሲል ኔቸር የተሰኘ ድረገጽ ላይ የወጣው ጥናት አመላክቷል። ይህን የጥናት ግኝት የጥርስ ህክምና ሀኪሙ ዶ/ር ሽመልስ ተኮላ ከአዲስ ስታናዳርድ አማርኛ ጋር በደረጉት ቆይታ እንደሚጋሩት ገልፀዋል፡፡
አዲሱ ተሻለ ስለሺ፣ ምትኩ ተስፋየ ወንድሙ እና እንዳሻው ሙለታ ፍቅሬ የተባሉ የዘርፉ ሙሁራን ባሳተሙት ጥናት ናይጀሪያ 14 ነጥብ 5 እና ሱዳን 15 ነጥብ 9 በመቶ በሆነ ነጥብ ከኢትዮጵያ ብዙም ባልተሻል ነገር ግን ከፍ ብለው የተቀመጡ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡ ጎረቤት ኬንያ እጅግ በተሻለ ሁኔታ 77 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ የጥርስ ንጽህናቸውን የሚጠብቁ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
የአለም የአፍ ንጽህና የተመለከተ በ2022 የወጣ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ከሆነ ከአፍ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ህመሞች ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊየን የሚሆን ህዝብ ይጠቃል። የጥርስ መበስበስ ዋነኛው የጥርስ ህመም ተደርጎ ይቆጠራል። የከተሞች መስፋፋት እና የአኗኗር ዘዴ እየተለወጠ መምጣት የጥርስ በሽታ እንዲጨምር እያደረጉት እንደሚገኝ በጥናቱ ተጠቁሟል። በቂ የውሃ አቅርቦት፣ የጥርስ መጠበቂያ ምርቶች አለመኖር፣ ከፍተኛ ስኳር መጠን ያላቸው ምግቦች በስፋት መቅረባቸው እና ሁሉም ሊያገኛቸው መቻሉ፣ ወደ ጥርስ ህክምና የመሄድ ልማድ አናሳ መሆን እና ሌሎች ምክንያቶ በአጠቃላይ ለችግሮቹ መንስኤ ከሆኑት መካከል ተጠቅሰዋል።
ጥንታዊ የሰው ልጅ የጥርስ ጤንነት አጠባበቅ
ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጅ የጥርስ ጤንነቱን ለመጠበቅ የተለያዩ መንገድን ይከተል እንደነበር የዘርፉ ሙሁራን ያሰፈሯቸው መዛግብት ያሳያሉ። በጥንት ግዜ በአንድ ወቅት ሽንት እንደ ጥርስ ማንጫ እና የአፍ ማጽጃ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበርም ይገለጻል።
የጥርስ ህምክምና ክሊንክ ባለቤት እና የዘርፉ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ሽመልስ ተኮላ የሰው ልጅ ከባቢሎን ዘመን ጀምሮ ባህላዊ በሆነ መንገድ ጥርሱን ማጽዳት መጀመሩን ከአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል። የጥርስ ማጽዳት ተግባሩ፣ የእንጨት ቅርፊቶችን ጨምሮ ቀጫጭን ስንጥሮችን በማኘክ እንደነበር ይገልጻሉ። በጥንታውያን ግሪክ እና ሮማውያን ደግሞ ላባ እና አጥንትን ጭምር እንደ ስንጥር (ቱዝፒክ) ይጠቀሙ ነበር ብለውናል። አፍን በማጉመጭመጭ ማጽዳት ደግሞ በቻይና ከ3700 አመት በፊት እንደተጀመረ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የጥርስ ንጽህና አጠባበቅ ባህል
“ባህላዊ የጥርስ ንፅህና አጠባበቅ መንገዱንም ጨምሮ የእኛ የኢትዮጵያውያን የጥርስ ንጽህና አጠባበቅ ልማድ እጅግ ዝቅተኛ ነው” ሲሉ የሚገልፁት የዘርፉ ባለሙያ ዶ/ር ሽመልስ የትኛውንም ዘዴ ይሁን ማለትም ዘመናዊ መንገድም ይሁን ባህላዊ የጥርስ ንጽህና አጠባበቅ ባህላችን እጅግ አናሳ መሆኑ መታረም ይገባል ብለዋል። ጥርሳችንን የምናጸዳው ደስ ሲለን ብቻ ነው የሚሉት ዶክተሩ ህክምናው እንደሚያዘው በቀን ሁለት ግዜ ጠዋት እና ማታ ከምግብ በኋላ ጥርስን የማፅዳት ልማድ የለንም ብለዋል።
ጥርስ በ24 ሰዓት ውስጥ ካልተፀዳ የማይለቁ ቆሻሻዎች ይኖራሉ ሲሉ የገለፁት ዶ/ር ሽመልስ ጥርስ የምናጸዳበትም ሰዓት ትክክል አይደለም ሲሉ የጥርስ ንፅህና አጠባበቅ ልማዳችንን ይተቻሉ። የህጻናት መዝሙር ሰምተህ ከሆነ ጠዋት ተነስቼ፣ ፊቴን እታጠብና፣ ጥርሴን አጸዳና፣ ቁርሴን በልቼ ነው የሚለው መዝሙር፤ መሆን ያለበት ቁርሴን በልቼ ጥርሴን አጸዳና…ነው ሲሉ በማሳያነት ያስቀምጣሉ።
ሐኪሙ “የግንዛቤ ችግር አለ፤ ብዙ ሰው ከእንቅልፉ እንደተነሳ ጠዋት ላይ ጥርስ መቦረሽን ነው የለመደው፤ ይህ ስህተት ነው፣ መሆን ያለበት ከቁርስ እና ከራት በኋላ ነው” በማለት መክረዋል።
ዶ/ር ሽመልስ እንደ ሀገር ያሉብን ዋነኛ ችግሮች የጥርስ መበስበስ እና የድድ ህመም ናቸው፤ መነቀልም ይሁን ሌሎች ችግሮች የሚመጡት ከነዚህ ሁለቱ ችግሮች ነው፤ ሁለቱም ደግሞ የንጽህና ችግር ዋነኛ መንስዔያቸው ነው ብለዋል።
ባህላዊ የጥርስ መፋቂያ
ሶስት ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች ያጠኑት እና ኔቸር ድረገጽ ላይ የወጣው ጥናት የተካሄደው አዲስ አበባን ዘጠኝ የሀገሪቱ ከተሞች ላይ ነው፡፡ በአዲስ አበባ በበርካታ ቦታዎች የጥርስ ህክምና ማዕከላት ከሌሎች የህክምና ማዕከላት በተሻለ እንደሚገኙ በተለያዩ የከተማ አከባቢዎች ተሰቅለው ከሚታዩ ማስታወቂያዎች መገንዘብ ይቻላል። ከጥርስ ህክምና መስጫ ክሊኒኮች በበለጠ ግን በስፋት የሚታየው የጥርስ መፋቂያ ይዘው የሚዞሩ ወጣቶች መበራከት ነው፤ በተለይ በአደባባዮች እና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች።
መገናኛ አደባባይ ላይ የጥርስ መፋቂያ በመሸጥ የሚተዳደረው መርከል ማሞ በአቅራቢያው ብቻ እስከ ስልሳ የሚደርሱ መፋቂያ የሚሸጡ ወጣቶች መኖራቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አማርኛ የዝግጅት ክፍል ገልጿል።
መገናኛ አከባቢ በሊስትሮነት ይተዳደር እንደነበር የሚገልፀው መርከል “በአዲስ አበባ ደንብ አስከባሪዎች በአካባቢው እንዳልሰራ በመከልከሌ ስራ አልነበረኝም፤ በኋላ ላይ በጓደኞቼ ግፊት መርካቶ በመሄድ የጥርስ መፋቂያዎቹን ገዝቼ እመጣና እዚህ መገናኛ አከባቢ በመሸጥ ገቢ ማግኘት ጀመርኩ” ሲል ታሪኩን ያጋራል።
አንድ መፋቂያ በሁለት ብር እንገዛዋለን፣ ስንሸጠው አምስት ብር ያወጣል ሲል ገልጾ በየሶስት ቀኑ መርካቶ እየሄድኩ በብዛት አመጣለሁ፤ ከማመጣው የጥርስ መፋቂያ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ብር ትርፋ አገኛለሁ፤ እራሴን እያስተዳደርኩ የተወሰነ እቆጥባለሁ ሲል ገልጿል።
የአዲስ አበባ ሰው በብዛት መፋቂያ ተጠቃሚ ነው ሲል የሚናገረው ይህ ወጣት ደንበኞቻችን “የጥር ሳሙና አፍ ያሸታል ይሉናል፤ እኛ የምንሸጠው መፋቂያ የተፈጥሮ በመሆኑ እና ምንም አይነት ኬሚካል ስለሌለው በብዙ ሰዎች ተመራጭ ነው” ሲል አስረድቷል። በተለይ ደግሞ ከጅማ የሚመጣው ቦቶሮ የሚባለው መፋቂያ ተመራጭ ነው፣ ከአከፋፋዮች አምስት ብር እንገዛዋለን ስንሸጠው ከአስር ብር እስከ ሃያ ብር ያወጣል በማለት ገልጿል።
ወሰን አለማየሁ የተባለ እድሜው 18 አመት እንደሆነው የገለጸልን ሳሊተምህረት አከባቢ ያገኘነው ወጣት በበኩሉ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ አንድ ወር ይሆነኛል፤ በቀን እስከ ሁለት መቶ ብር እሸጣለሁ፤ ገና ጀማሪ ስለሆንኩ እንጂ ብዙ ጓደኞቼ ከኔ በላይ ይሸጣሉ፣ እነሱ ንግዱን ለምደውታል ሲል ገልጿል።
ባህላዊ ጥርስ መፋቂያ ጉዳት አለውን?
በሀገራችን በብዛት ለጥርስ ንጽህና መጠበቂያ ጥቅም ላይ የሚውለው ከተለያዩ ዛፎች የሚገኝ ቀጫጭን የመፋቂያ እንጨቶች ናቸው። የጥርስ መፋቂያ መጠቀም በዋነኝነት የምንገለገለው ጥርስን ለማጽዳት ብቻ በሚል ነው ሲሉ የገለጹልን ዶ/ር ሽመልስ የጥርስ ጤንነት አጠባበቃችን አነስተኛ ቢሆንም ጨርሶ ከመወቀስ ያተረፈን ግን የጥርስ መፋቂ ተጠቃሚ ቁጥር ብዙ በመሆኑ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
እንደ ዘመናዊ የጥርስ ብሩሽ ሙሉ ጥቅም ባይኖረውም መፋቂያ መጠቀምን ማበረታታት እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ እንዲሁ በዘፈቀደ ያልኩት ሳይሆን ጥናቶችም ተደርገዋል ሲሉ ይገልጻሉ። “አንዳንድ ጥናቶች የሚያሳዩት በርካታ ከተክሎች የሚገኙ የመፋቂያ አይነቶች ጸረ ባክቴሪያ እና ጸረ ፈንገስ የተፈጥሮ ንጥረ ነገር ያላቸው መሆናቸውን ነው” ያሉት ዶ/ር ሽመልስ በአንቦ አከባቢ በተደረገ ጥናት በአከባቢው ማህበረሰብ ጥቅም ላይ የሚውሉ መፋቂያዎች ቶክሲክ ባህሪ እንደሌላቸው ተረጋግጧል፤ በአብዘሃኛዎቹ መፋቂያዎች ጎጂ የሆነ ንጥረ ነገር የላቸውም ብለዋል።
ዋናው ነጥብ ማጽዳት መቻሉ ነው የሚታየው፤ መርዛማነት እና ጎጂ ካልሆነ ችግር የለውም ሲሉ አብራርተው እንደ ዘመናዊ የጥርስ ብሩሽ ድድ ላይ እና በአንዳንድ የጥርስ ክፍሎች ላይ ያሉ ቆሻሻዎችን ላያጸዳ እንደሚችል ግን መረዳት ያስፈልጋል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል። መፋቂያ ጥርስን ብቻ ነው የሚያጸዳው፤ ዘመናዊ የጥርስ ብሩሽ ግን ድድንም ስለሚያጸዳ ብቻ ሳይሆን ስለሚያሸውም የደም ዝውውርን ጤናማ ያደርጋል፤ ምላስ ለማጽዳት ከመፋቂያ ይልቅ ብሩሽ ይቀላል ብለዋል።
በአግባቡ በመደበኛ ደረጃ፣ በየግዜው መፋቂያ የምንጠቀም ከሆነ መልካም ነው፤ የሚበረታታ ነው ያሉት ባለሞያው በኢትዮጵያ ስንመለከተው ፋርማሲ ወይም ሱፐርማርኬት ገብቶ የጥርስ ሳሙና እና ብሩሽ ከሚገዛው ይልቀ በየመንገዱ መፋቂያ ገዝቶ የሚጠቀመው እንደሚበዛ ጥርጥር የለውም፤ ይህም ቢሆን ግን የሚበረታታ ነው፤ ይሄ ልማድ ነው ወደ ዘመናዊ መንገድ ወደ ጥርስ ብሩሽ የሚመራው ነማት አስረድቷል።
ጥርስ ንቅሳት
ከዚህ ጋር አያይዘውም ጥርስን መነቀስ እንደማንኛውም ጎጂ ባህል ሊወሰድ የሚገባው እንጂ ምንም አይነት የሚሰጠው ጥቅም የለም ያሉን ዶ/ር ሽመልስ፣ ቀለም ወይንም ካርቦን የተባለ ጎጂ ንጥረ ነገር ተጠቅሞ የድድን ክፍል ህዋስ በመግደል ጠባሳ እንደማሳረፍ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል። አስ