በሚሊዮን በየነ @millionbeyene
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25/ 2015 ዓ.ም ፡- በጳውሎስ ሆስፒታል የልብ ህክምና ክፍል ተቋቁሞ ህክምና መስጠት ከጀመረ አምስተኛ አመቱን ሊይዝ ተቃርቧል፡፡ እስካሁን ከ1500 በላይ ለሚሆኑ የልብ ታማሚዎች ህክምና አገልግሎት መስጠቱን የሚገልፁት የሆስፒታሉ የልብ ህክምና ክፍል ዋና ሃላፊው ዶ/ር ሰይፉ ባጫ አገልግሎቱን ከጀመርን ወዲህ ከሁሉም አይነት ዘርፍ ህክምና ሰጥተናል/ፕሮሲጀር ሰርተናል/ ይላሉ።
ሁሉም ህክምናው የሚሰጠው በመንግስት ወጪ “በነጻ ያለምንም ክፍያ” መሆኑን የነገሩን ዶ/ር ሰይፉ “እዚህ በነጻ የምንሰጣቸው ህክምናዎች በግል ሆስፒታሎች እስከ 300ሺ የሚያስወጡ አሉ እንደ ፔስሜከር አይነቶቹ ፤ በደም ስር ገብተን የምናሰፋው ቫልቭ ተከፍቶ ቢሰራ ከ400ሺ በላይ ወጪ ሊያስጠይቅ ይችላል” ሲሉ ጠቁመዋል።
በጳውሎስ ሆስፒታል የልብ ህክምና ክፍል ለመታከም ሲጠባበቅ ያገኘነው ታሪኩ ሽጉጤ የተባለ የአዲስ አበባ ነዋሪ ‘’ድንገት የህመም ስሜት ተሰማኝ፣ መቆም አቃተኝ፣ ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተወሰድኩ፤ በተደረገልኝ ምርመራ የልብ ህመም እንዳለብኝ አወኩ‘’ ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ይገልጻል።
ኢብራሂም ንጋቱ የተባለ ጀሞ ሁለት በሚል ከሚጠራ የአዲስ አበባ አከባቢ እንደመጣ የነገርን ታማሚ በበኩሉ “የልብ ህመም የሚባል ነገር አለብኝ የሚል ግምት ኖሮኝ አያውቅም፤ በሽታየ አስም ነው፣ እሱ እንዳለብኝ ብቻ ነው የማውቀው፤ ከአስር ቀን በፊት ነበር ህመሙ የጀመረኝ፤ ወደ ጳውሎስ ተወስጄ በጳውሎስ ሀክምና ሳደርግ ቆይቼ ነው የቀዶ ህክምና የተደረገልኝ” ሲል ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።
ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች ስንጠይቃቸው የሚነግሩን ተመሳሳይ ታሪክ ነው ሲሉ የልብ በሽታ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ማሩ ሰግዴ ያስረዳሉ። በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ የልብ ህመም በአስደንጋጭ ሁኔታ እያደገ መሄዱን የገለጹልን ዶ/ር ማሩ የበረታ ህመም ካልተሰማን በስተቀር ወደ ህክምና ቦታ በመሄድ የጤንነት ሁኔታን የመከታተል ቸክአፕ ባህል ስለሌለን ለድንገተኛ አደጋ የተጋለጥን ነን ሲሉ ገልጸዋል። የልብ ህመም በሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል፤ ለበርካቶችም የሞት ምክንያት ሁኗል ሲሉ ገልጸውልናል። ከታዋቂ ሰዎች እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ክፍል ድረስ በተደጋጋሚ የሚሰማው ብሶት ማለትም ለህክምና ወደ ሆስፒታል መኪናውን እያሽከረከረ ሂዶ አስከሬኑ ወጣ፣ ወይንም በሰላም ከቤት ወጥቶ አሞኛል ልታከም ብሎ ክሊኒክ ገብቶ ወደቀ ከዚያም ወዲያውኑ መድሃኒት ሰጡት እና ሞተ የሚሉ ብሶቶች ቢጠኑ አብዛኛዎቹ ከልብ በሽታ ጋር የተያያዙ ናቸው ሲሉ ዶ/ር ማሩ ይሞግታሉ።
ከሌላው አለም አንጻር በካት ምርመራ እና ህክምና የመጨረሻ ውስብስብ የሚባለው ኢፒስተዲ (An electrophysiology (EP) study) የሚባለው ራድዮ ፍሪኮንሲ አቭሌሽን (Radiofrequency ablation) በቅርቡ የጀመርነው ነው፤ ይሄኛው ላይ የሰለጠነ የሰው ሃይል ይጎለናል፤ እቃዎቹን ግን አሟልተናል ብለውናል ዶ/ር ሰይፉ። ከዚያ በተረፈ ሌሎች እጅግ የተራቀቁ ቀዶ ጥገና ሳይሰራ ዲቫይስ ክሎዠር የሚባሉ አሉ እሱን በቅርቡ የመጀመር ዕቅድ አለን ሲሉም ነግረውናል። በካትላብ ደረጃ ብዙ ቀረብን የምንለው የለም፣ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነውም ብለዋል።
ህክምናውን እንደልብ ለመስጠት ያላስቻለው ምክኒያት
የልብ ህክምና አገልግሎት የምንሰጥባቸው መገልገያ መሳሪያዎች በተመለከተ በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን ሲሉ የገለጹልን ሰይፉ ባጫ (ዶ/ር) ዋናው ሲቋቋም የመጡ ማሽኖች ናቸው (ካትላብ የሚባለው)፣ ትልቁ ወጪ እሱ ነው፤ በመቶ ሚሊየኖች የሚገዛ ነው፤ ማሽኑ ሰርቪስ ከተደረገ ረጅም ግዜ ያገለግላል ብለዋል።
ሁለተኛው መገልገያ መሳሪያዎቻችን የተወሰነ አገልግሎት የሚሰጡ አላቂ የሆኑት ሲሆን ምናልባት አንዱ መገልገያ መሳሪያ ለአንድ ሰው ብቻ ወይንም አንዱ እቃ ለሁለት እና ሶሰት ሰው ብቻ የሚያገለግለው ነው። አንዳንዶቹን መገልገያዎች አንድ ግዜ ተጠቅመህ መጣል ሊኖርብህ ይችላል፤ እነዚህ ላይ ነው ከባድ ማነቆ ያለብን ሲሉ ያስታወቁት ሃለፊው ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ከውጭ የሚመጡ በመሆናቸው ከዶላር እጥረት ጋር በተያያዘ እንደልብ ማግኘት ስለማይቻል መሆኑን ጠቁመዋል። በእርዳታ ከሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች ካላገኘን በእጥረት ሳቢያ ፕሮሲጀር ላንሰራ እንችላለን ሲሉ አስታውቀው ለአጠቃላይ ስራቸው ማነቆ የሆነባቸው እሱ መሆኑን አመላክተዋል።
አላቂ እቃዎቹ ካሉን ብዙ ሰዎችን ማዳን እንችላለን፣ እቃዎቹ ሲኖሩን አስር ሰው በሳምንት ፕሮሲጀር እንሰራለን፣ እቃዎቹ ከሌሉን ደግሞ ሁለትም አንድም ብቻ እንሰራለን ሲሉ የአላቂ ህክምና መገልገያ እቃዎቹን ወሳኝነት አስረድተዋል።
የልብ ህክምና ግዜ የሚሰጥ አይደለም፣ ኢመርጀንሲ ነው፤ ብዙዎቹ በአጭር ቀጠሮ የሚሰጡ ናቸው ሲሉ ገልጸው ምርመራውን ወዲያውኑ ህመሙ እንደጀመረው እንሰጣለን፣ አብዛኛውን እንዴሎች ህመሞች አሰልፈን፣ ወረፋ አስይዘን አንሰራም ብለዋል።
ከልብ ህመሞች መካከል የተወሰኑት ጊዜ የሚሰጡ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶ/ር ሰይፉ ባጫ ለምሳሌ ቫልቮቶሚ የሚባለው አንዱ ነው፤ በዛ ከተባለ በወር አነሰ ሲባል በሳምንት ይሰራል ብለዋል። ፔስሜከር የሚባለው የልብ ባትሪ ግን ሶስት ወርም ስድስት ወርም እቃው እስኪመጣ ድረስ የሚጠብቁ አሉ ብለው ይህም የሚሆነው የእቃው እጥረት ስላለብን ብቻ እና ብቻ ነው ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል። በህክምና መስጫው ክፍል ወረፋ የያዙ እስከ ሃምሳ የሚሆኑ መኖራቸውን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ አንዳንዶቹ ስድስት ወር የጠበቁ መኖራቸውን እና ወረፋ ከያዙት ውስጥ በመሃል ስልክ ደውለን ለመጥራት ስንሞክር ህይወታቸው አለፉ እንባላለን ብለዋል። ሌሎቹን የልብ ህክምናዎቹን ግን ብዙም ወረፋ እንደማያስጠብቁ ገልጸውልናል።
250 የህሙማን አልጋ ያለው ፓውሎስ ሆስፒታሉ ውስጥ የተገነባው የልብ እስፔሻሊቲ ህክምና መስጫ ህንጻው መገባደዱን እና በቅርቡ እንደሚመረቅ የነገሩን ዶ/ር ሰይፉ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ አገልግሎት ይሰጣል የሚል እቅድ መያዙን አስታውቀዋል። አጠቃላይ ሁሉም ነገር እስኪያልቅ በሚል ለጊዜው የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጴጥሮስ ሆስፒታል የልብ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ጳውሎስ ሆስፒታል ከተመሰረተ 75ኛ አመቱን ያስቆጠረ ቢሆንም በስሩ የሚገኘው የልብ ህክምና መስጫ ማዕከል ደግሞ ስራ ከጀመረ አምስት አመታትን ብቻ ማስቆጠሩን ዋና ሃላፊው ዶ/ር ሰይፉ ባጫ አስታውቀዋል።
የሰለጠነ የሰው ሃይልን በተመለከተ ሁሉም የህክምና አገልግሎቶቹ የሚሰጡት በአስር ዶክተሮች እና 14 ነርሶች መሆኑን የነገሩን ሃላፊው ሁሉም የህክምና ባለሞያዎች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እና እዚሁ የሰለጠኑ እና በተጨማሪም ወደውጭ ተልከው ስልጠና የወሰዱም መኖራቸውን ነግረውናል። በተለያዩ ግዜያት ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ባለሞያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማካሄድ እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚመጡም አስታውቀዋል፤ በቅርቡ ከአውስትራልያ፣ ከፈረንሳይ እና ከስዊዘርላንድ መጥተው እንደነበር ገልጸዋል። በዚህም በርካታ ድጋፍ እና የክህሎት ሽግግር መደረጉን ጠቁመዋል። አስ