ዜና ፡ ባለፉት 21 ወራት በኢትዮጵያ በኩፍኝ ወረርሽኝ ሳቢያ 182 ሰዎች መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

ፎቶ – UNICEF Ethiopia

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30/2015 ዓ.ም፡- ባለፉት 21 ወራት በኢትዮጵያ በኩፍኝ ወረርሽኝ ሳቢያ 182 ሰዎች መሞታቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡ ድርጅቱ ከጥቂት ቀናት ብፊት ይፋ ባደረገው መግለጫ የኩፍኝ በሽታ በኢትዮጵያ በየአመቱ በወረርሽኝ ደረጃ እንደሚከሰት ገልፆ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ወረርሽኙ ሪፖርት መደረጉን እና ከ16ሺ በላይ በሆኑ ሰዎች በተደረገ የላበራቶሪ ምርመራ መረጋገጡን አስታውቋል። 

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2021 በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች 1, 953 ሲሆን ይህም በ2022 በ375 በመቶ በመጨመር 9, 291 ሰዎች ተጠቅተዋል፤ በ2023 ደግሞ 6, 933 ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡

ይህም በ2021 ከተመዘገበው የወረርሽኙ ተጠቂ አምስት እጥፍ የሚሆን ተጠቂ በ2022 መመዝገቡን የአለም የጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል። ይህም ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ምን ያክል እየተስፋፋ እንደመጣ ማሳያ ነው ብሏል።

ለወረርሽኙ መጨመር የህዝቡ በሽታ የመቋቋም አቅም አነስተኛ መሆን፣ ግጭት፣ በሀይል ከቀየ መፈናቀለ እና ሌሎች ሰብአዊ ቀውሶች ህጻናት ክትባቱን እንዳይወስዱ ማድረግን በምክንያትነት አስቀምጧል። 

በ2022 ከተመዘገበው የኩፍኝ ወረርሽኝ ተጠቂዎች ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት አመት በታች እድሜ ያላቸው መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል። በኢትዮጵያ ወረርሽኙ በአሁኑ ወቅት በስምንት ክልሎች በሚገኙ 44 ወረዳዎች  ውስጥ መኖሩን የአለም የጤና ድርጅት በሪፖርቱ አካቷል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.