ዜና፡ የጤና ሚንስቴር ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ ማብቃቱን ገለፀ፤ አዲስ የበሽታው ዝርያ ሊከሰት እንደሚችል አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 30/2015 ዓ.ም፡- የጤና ሚንስቴር ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ ማብቃቱን ገልፆ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሳርስ ኮቪድ-2 (SARS COV-2) የሚያዙና የሚሞቱ ሊኖሩ እንደሚችሉ እንዲሁም አዲስ የበሽታው ዝርያ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት እንዳለ አስታወቀ፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ አብቅቶ እንደ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሆኖ ይቀጥላል ማለቱን ተከትሎ የጤና ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያም በአሁኑ ሰዓት በበሽታው የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የድነገተኛ ጤና ስጋትነቱ ማብቃቱን ገልጧል፡፡

ነገር ግን በሳርስ ኮቪድ-2 (SARS COV-2) የሚያዙና የሚሞቱ ሊኖሩ እንደሚችሉ እንዲሁም አዲስ የበሽታው ዝርያ ሊከሰት እንደሚችል ስጋት እንዳለ ማሳሰብ እወዳለው ያለው ሚንስቴሩ ይህንንም ለመግታት ተከታይነት ያለው ጥረት ማድረጉ ይቀጥላል ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ታካሚ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 27፣ 2015 ድረስ ከ5.5 ሚሊዮን በላይ የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት በበሽታው መያዛቸውን ያስታወቀው መግለጫው 7574 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ገልጧል፡፡ በተጨማሪም በፅኑ ታመው ካገገሙ መካከል 6 በመቶ የሚሆኑት ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የጤና እክል አጋጥሟቸዋል ሲል ገልጧል፡፡

ሚያዚያ 27 የዓለም ጤና ድርጅትዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም የበሽታው ድንገተኛ ስጋትነቱ ማብቃቱን በባሰሩበት መግለጫ፣ ወረርሽኙ በዓለም ዙሪያ በትንሹ የ20 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ገልፀዋል።

ዶ/ርቴዎድሮስ በመግለጫቸው የበሽታው ድንገተኛ ስጋትነቱ አብቅቷል ማለት በሽታው የደቀነው የጤና ስጋት ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት አለመሆኑን ጠቁመው በሽታው ዳግም የሚባባስ ከሆን ግን አስቸኳይ የጤና አደጋ ተብሎ የሚታወጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.