አዲስ አበባ፣ጥቅምት29/ 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በኮንሶ ዞን እና በሦስት ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሰረት በማድረግ ከሐምሌ 24 እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ክትትል በማከናወን ያዘጋጀውን 21 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በኮንሶ ዞን፣ በአሌ ልዩ ወረዳ፣ በዲራሼ ልዩ ወረዳ እና በአማሮ ልዩ ወረዳ በሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎችና ተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር በመዘዋወር፣ ተፈናቃዮችን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን፣ የተለያዩ ድጋፍ የሚያቀርቡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን አነጋግሯል፣ የቡድን ውይይቶችን አከናውኗል፣ የሰነድ ማስረጃዎች አሰባስቧል፣ የአካል ምልከታም አድርጓል፡፡
በክትትሉ በኮንሶ ዞን፣ ካራት ዙሪያ እና ሰገን ዙሪያ ወረዳዎች በሚገኙ 3 ቀበሌዎች በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮች፣ ከአሌ ልዩ ወረዳ ቀርቀርቴ ቀበሌ ተፈናቅለው በደቡብ ኦሞ ዞን በናጸማይ ወረዳ እጨቴ ቀበሌ ቴሌ ታወር፣ እንዲሁም በአማሮ ልዩ ወረዳ በኬሌ ቀበሌ እና በአማሮ ኬሌ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ተሸፍነዋል፡፡ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች በአጠቃለይ የተመዘገቡ 145,933 የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል 53,400 ተፈናቃዮች በኮንሶ፣ 40,000 ተፈናቃዮች በዲራሼ፣ 8,331 ተፈናቃዮች በአሌ እና 44,202 ተፈናቃዮች በአማሮ የሚገኙ መሆኑም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡
ኮሚሽኑ የክትትል ሥራውን ያከናወነው አግባብነት ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች በመጠቀም በተዘጋጁ መለኪያዎች፣ መጠይቆችና መመሪያዎች ላይ በመመስረት ነው፡፡ በዚህ የክትትል ሂደት በአጠቃላይ ጾታን፣ ዕድሜን እና የአካል ጉዳትን መሰረት ያደረጉ 18 የቡድን ውይይቶችን ከተፈናቃዮች ጋር ያደረገ ሲሆን ከሚመለከታቸው 25 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከ10 መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይቶችን እና ቃለ መጠይቆችን በማድረግ እንዲሁም የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብና በመጠለያ ጣቢያዎቹም ምልከታ በማድረግ መረጃና ማስረጃዎችን ሰብስቧል፡፡ በተጨማሪም ኮሚሽኑ በክትትሉ ግኝቶች ዙሪያ ለመወያያት እና ምክረ ሃሳቦቹ እንዲፈጸሙ ለመወትወት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ከነሐሴ 23 እስከ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ባከናወነው የምክክር መድረክ ተጨማሪ መረጃዎች በመሰብሰብ ሪፖርቱን ማዳበር ችሏል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በኮንሶ ዞን እና በአጎራባች ልዩ ወረዳዎች መፈናቀል ስለተከሰተበት አውድ እና አጀማመር እንዲሁም የተደጋጋሚ መፈናቀል መንስዔዎች እና በተፈናቃዮቹ ላይ ያስከተለውን የሰብአዊ መብቶች ተጽዕኖ ለይቷል፡፡ በመፈናቀሉ እና በመፈናቀል ሂደት የደረሱ የመብቶች ጥሰት፣ ከመፈናቀል በኋላም በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የተስተዋሉት ክፍተቶች፣ በተለይም በምዝገባ እና ሰነድ ማግኘት፣ የፀጥታ እና ደኅንነት፣ እንዲሁም ፍትሕ ማግኘት፣ ሰብአዊ ድጋፍ ማግኘት፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ዘላቂ መፍትሔዎች ማመቻቸት በሪፖርቱ የተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው።
ተፈናቃዮች በግጭት እና በመፈናቀል ሂደት ወቅት የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የደረሰባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሞቱና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸው፣ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት መፈጸሙ፣ የአካል አቅማቸው የተዳከመ አረጋውያን እና ለመሸሽ ያልቻሉ አካል ጉዳተኞች ላይ ድብደባ እና እንግልት መድረሱ፣ እንዲሁም ቤቶቻቸው፣ ንብረቶቻቸው፣ ከብቶቻቸው እና ሰብሎቻቸው መውደማቸውና መዘረፋቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድን በሚመለከት በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖሩን እንዲሁም የመታወቂያ ካርድን ጨምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎት አለመኖሩ በተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ አካቷል፡፡
ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያ ጣቢያዎች አካባቢ በቂ ጥበቃ ካለመኖሩ የተነሳ ተፈናቃዮች የደኅንነት ሥጋት እንዳለባቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ የሆነ የሰብአዊ ድጋፍ እንደማይቀርብ እና በዚህም የተነሳ ተፈናቃዮች ለሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸው፣ የምግብ እጥረት ምልክቶች በሕፃናት እና በአጥቢ እናቶች ላይ መስተዋሉ፣ ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ባለመዝነቡ በተፈጠረው ድርቅ እና በአካባቢው በነበረው ተከታታይ ግጭት ምክንያት የእርሻ ሥራ በመስተጓጎሉ የምግብ እጥረት መከሰቱ፤ በዚህም የረሀብ ሥጋት መኖሩ ተመላክቷል፡፡
የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን በተመለከተ የመጠለያ ቦታን ጨምሮ ሌሎች ምግብ-ነክ ያልሆኑ የመገልገያ ቁሳቁሶች ለሁሉም ተፈናቃዮች ተደራሽ አለመሆናቸው እና የሕክምና ድጋፍ የሚያደርጉ የተራድዖ ድርጅቶች ተደራሽ አለመሆን ከተለዩት ክፍተቶች መካከል ናቸው፡፡ እንዲሁም በመንግሥት የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠየቀውን ክፍያ ለመክፈል ባለመቻል ምክንያት ለሕክምና እጦት እና ለጤና ቀውስ የተዳረጉ ተፈናቃዮች መኖራቸው ተካተዋል፡፡ ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችን ማለትም ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በቂ እና ፍላጎታቸውን ያማከለ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው፤ በተለይም ሴቶች ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ዘላቂ መፍትሔን አስመልክቶ መንግሥት በቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው አስተማማኝ ፀጥታና ደኅንነት በማረጋገጥ እና መደበኛ ኑሮ ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ በመፍጠር ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው የጠየቁ ተፈናቃዮች ቢኖሩም ይህንን ለማሳካት የሚያስችል የፀጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ መመለስ አለመቻላቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡ በአንጻሩ ተፈናቅለው በሚገኙበት ወረዳ መንግሥት በቋሚነት የመኖሪያና የእርሻ ቦታ ሰጥቷቸው መኖር የሚፈልጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸውን በክትትል ሪፖርቱ አካቷል፡፡
ኢትዮጵያ የካምፓላ ስምምነት አባል ሀገር እንደመሆኗ፤ መንግሥት በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ የሰነድና ምዝገባ፣ የፀጥታና ደኅንነት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነት እና ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍና መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት እንዲሁም ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ማሻሻል እንደሚገባ እና በአካባቢው ለተደጋጋሚ መፈናቀል መንስዔ ለሆኑ ጉዳዮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያፈላልግ እንደሚገባ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል።
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተገቢውን የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ በቂ የሕግና ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ የተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የከፋ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡ አክለውም “ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በቂ የሰብአዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ከመሆኑም ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት በዚህ አካባቢ የሚያገረሹ ግጭቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ለተደራራቢ ጉዳት እና መፈናቀል እየዳረጉ ስለሆነ ለመፈናቀል መንስዔ የሆኑ ግጭቶችን ማስወገድ፣ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ እና ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው” በማለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ ያገኙ ዘንድ በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢሰመኮ