በሚሊዮን በየነ @MillionBeyene
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29/2015 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በዘንድሮ የክረምት ወቅትየዛፍ አንበጣ ስጋት ሊኖር እንደሚችል በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የኢትዮጵያ ቁጥጥር ቅርንጫፍ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቀ፡፡
በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የኢትዮጵያ ቁጥጥር ቅርንጫፍ ቢሮ ሃላፊ ሒወት ለማ በተለይ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በኢትዮጵያየዛፍ አንበጣ ስጋት ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው የበረሃ አንበጣ ስጋት ግን የለም ብለዋል። የዛፍ አንበጣ ሁልጊዜ አለ ያሉት ሃላፊዋ በተለይ በትግራይ፣ አፋር፣ ሶማሌ የተለመደ መሆኑን አስታውቀዋል።
በምስራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት በዘንድሮ የክረምት ወቅት ምንም አይነት የበረሃ አንበጣ ስጋት የለም ሲል ገልፆ ነገር ግን ሌሎች የሰብል ተባዮች ፈተና መሆናቸውን አስጠንቅቋል።
የበረሃ አንበጣ እና የዛፍ አንበጣ አውዳሚነታቸው ምንም አይገናኝም ሲሉ በንጽጽር የገለጹልን ሒወት የዛፍ አንበጣ የመኖ ዛፎችን ጨምሮ በመመገብ ጉዳት ቢያስከትልም እንደ በረሃ አንበጣ በመንጋ ተከስቶ ትልቅ ውድመት ያስከትላል ማለት አለመሆኑን ገልጸዋል። የዛፍ ላይ አንበጣ ሁልጊዜ አለ፣ ዛፎችን ይበላል፤ የበረሃ አነበጣ ግን ሲመጣ የፍራፍሬ ዛፎችን ጨምሮ ማንኛውንም አረንጓዴ ነገር ያጠፋል ብለዋል።
ከአንበጣ ውጭ ምን ስጋት አለ
በኢትዮጵያ ከበረሃ አንበጣ ውጭ ሌሎች ተባዮች ከፍተኛ ስጋት መሆናቸውን የገለጹልን ሒወት ለማ ለምሳሌ አፍሪካን አርሚ ዎርም ማለትም ተምች ዋነኛ መሆኑን አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ተምች ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል ያሉን ሃላፊዋ አማራ ክልል፣ ደቡብ ክልል፣ ኦሮምያ ክልል ሶስቱም ላይ እህል ከቡቃያ ጀምሮ እያጠፋ እንደነበረ በማሳያነት አቅርበዋል።
አሁናዊ ስጋቱ
ተምች ከደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል እንደሚጀምር የገለጹልን ሒወት ለማ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እያለ እየተሰደደ ኢትዮጵያ ይደርሳል ብለዋል። በኢትዮጵያ በተለመደ ሁኔታ ጥር ካልሆነ ደግሞ የካቲት እና መጋቢት ላይ እንደሚከሰት ጠቁመው አመች የአየር ሁኔታ ለምሳሌ አምስት ሚሊሜትር ብቻ እንኳን ዝናብ ከዘነበ እና እጽዋት አረንጓዴ ከሆኑ እና የሳትራቷ በአከባቢው ከደረሰች እንቁላሏን በመጣል ተምች እንደሚፈለፈል አስታውቀዋል።
ይህ ሂደት በኢትዮጵያ ክትትል የሚደረግበት መንገድ ማለትም ወጥመድ መኖሩን የነገሩን ሃላፊዋ ወጥመዱን ከጥር ወር ጀምረን እንሰቅላለን፤ ማህበረሰብ አቀፍ የሆነ ላለፉት 15 አመታት ሲሰራበት የነበረ ሲስተም መሆኑን ገልጸዋል። ሁኔታውን እራሱ ገበሬው ይከታተላል፣ ያያል በዚያ ሳምንታት ውስጥ አምስት ሚሊሜትር ያክል የሚሆን ዝናብ ከዘነበ እና እጽዋት አረንጓዴ ከሆኑ በሳምንት ውስጥ የተምች ትሉ ሊፈለፈል ይችላል፤ ጉዳት የሚያደርሰው ትሉ በመሆኑ ትኩረት የምናደርገው በትሉ ላይ ነው ብለዋል።
የተምች ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ደቡብ ላይ እንደሚጀምር እና በወራት ውስጥ ወደ ሰሜን የሀገራችን ክፍል ላይ እንደሚደርስ ያስታወቁት ሒወት በአሁኑ ወቅት አማራ ክልልን እየጨረሰ በመሆኑ ወደ ትግራይ መስፋፋቱ አይቀር ከዚያም ወደ ኤርትራ ያቀናል ሲሉ ገልጸዋል። አሁን ትግራይ ላይ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መረጃ እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
የተባይ ስጋት በትግራይ
የትግራይ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን ወልዱ በትግራይ የተባይ ወረርሽኝ ፈታኝ መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልፀዋል፡፡ በክልሉ ተከስቶ የነበረው የዛፍ አንበጣ እና ተምች ያስከተለው ጉዳት ለመግለጽ አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸው፣ ክልሉ ካለበት ወቅታዊ ችግር ጋር ተደማምሮ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን አመላክተዋል።
በትግራይ የዛፍ አንበጣ ያለበት ሁኔታ
አቶ መብራህቶም ስለ የዛፍ ላይ አንበጣ ሁኔታ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በክልሉ በርካታ ዞኖች በተበታተነ ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር እና ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ገልጸዋል። የዛፍ አንበጣ በጣም አውዳሚ ነው ያሉት መብራህቶም በሚያዚያ ወር ተከስቶ የነበረው የዛፍ አንበጣ በተለይ በሽሬ አከባቢ ብዙ ነገር ማውደሙን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በዚያ አከባቢ የነበረ የእንስሳት መኖ ሁሉንም በልቶ አጥፍቶታል፣ በበጋ ወቅት ለእንስሳ መኖነት የምንጠቀመው አረንጓዴ ቅጠል ነው፤ ሁሉንም እንዳለ ነው ያወደመው ሲሉ ገልጸው የእንስሳ መኖን ብቻ ሳይሆን በአከባቢው የነበረውን አትክልት እና ፍራፍሬ ሳይቀር አውድሞ ባዶ ነው ያስቀረን ብለዋል።
አሁንም አንበጣው በትግራይ በተበታተነ መልኩ እየተፈለፈለ ነው፣ በአጎራባች ክልል አፋር ለትግራይ 17ኪሜ ቅርብ ላይ ግን በመንጋ እየተፈለፈለ መሆኑን መረጃ ደርሶናል ያሉት መብራህቶም “አሳሳቢውም ይሄው ነው፣ ምክንያቱም ወደ እኛ ነው ቀጥታ የሚመጣው፤ ለፌደራል መንግስት አሳውቀናል፤ በአጎራባች ወረዳዎች እየተፈለፈለ ነው ተብሎ ከተነገረን ሁለት ሳምንተ ሁኖታል፣ በአንድ ወር መብረር ይጀምራል” ሲሉ ጭንቀታቸውን አጋርተውናል።
ተምችን በተመለከተ
አሁን እጅግ ያስቸገረን የተምች መስፋፋት ነው ያሉን ዳይሬክተሩ በትግራይ ክልል በጣም በስፋት መከሰቱን አስታውቀዋል። በሁሉም የትግራይ አከባቢ፣ ከጫፍ ጫፍ አለ ያሉን መብራህቶም በአሁኑ ወቅት በጣም ያስቸገረን እሱ ነው፤ ማሽላ እና በቆሎ ባለበት ሁሉ በጣም እያጠቃ መሆኑን አስታውቀዋል። ተምች በትግራይ በስፋት መከሰቱን ለፌደራል መንግስትም ይሁን በግብርና ቢሮ ላሉት የፋኦ(FAO) ተወካዮች አሳውቀናል ያሉት መብራህቶም ገብረኪዳን በደቡባዊ ትግራይ ራያ ዞን በሁሉም ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ ነበረ፤ አሁን የተወሰነ የመቀነስ አዝማሚያ አለው ብለዋል። በደቡብ በኩል የመቀነስ ነገር እንዳሳየ ሁሉ በማዕከላዊ ዞን በተለይ በሽሬ አከባቢ እየሰፋ፣ እየበዛ መሄዱን እና በስፋት መሰራጭቱን ገልጸዋል።
ለመከላከል የተደረገ ጥረት
ሁሉንም ተባዮች ባይሆንም በተለይ ተምችን ለመከላከል የተወሰነ ጥረት አድርገናል ያሉን መብራህቶም በክልሉ የተወሰነ የኬሚካል ክምችት እንደነበረ ጠቁመው እሱን ተጠቅመን ለመከላከለ የቻልነውን ያክል ሞክረናል ብለዋል። በተለይ አዲሱ መጤ የሆነውን ተምች ለመከላከል እጅግ አስቸጋሪ ነው ያሉት አቶ መብራህቱ ምክንያቱም በትግራይ ክልል ከጫፍ ጫፍ ስለሆነ የተከሰተው ምንም አቅመ የለንም ሲሉ አመላክተዋል። ከፌደራልም ይሁን ከለጋሽ ድርጅቶች የተሰጣቸው ምንም አይነተ ድጋፍ አለመኖሩን አስታውቀው በዚህም ምክንያት ተባዮቹን ለመከላከል ይረዳቸው ዘንድ በወረዳ ደረጃም ይሁን ለአርሶ አደሩ የሰጠነው ድጋፍ የለም ሲሉ ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ በራሱ አማራጮች ለመከላከል ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ለአዲስ ስታንዳረድ ያስታወቁት አቶ መብራህቶም አርሶ አደሩ በባህላዊ መንገድ በተለይም በሰው ሀይል ለቀማ በማከናወን ለመከለከል እየሞከረ መሆኑን ነግረውናል። አቅም ያለው አርሶ አደር ደግሞ በራሱ ወጪ ኬሚካል ገዝቶ በመርጨት ለመከላከል እየጣር እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አስ