በብሩክ አለሙ እና ጌታሁን ፀጋዬ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6/2014 ዓ.ም፡- ከደሴ ከተማ፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም ዋግ ኽምራ ዞን ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞች አዲስ አበባ ለመግባት በኦሮሚያ ክልል ሸኖ ከተማ ሲደርሱ የአዲስ አበባ መታወቂያ ካልያዛችሁ ማለፍ አትችሉም በሚል ምክኒያት ለከፍተኛ እንግልትና መጉላላት መዳረጋቸውን የደቡብ ወሎ ኮሙኒኬሽን አስታወቀ። በተመሳሳይ ምክኒያት ከደብረ ብርሃን-አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡም ተገልጿል፡፡
ተጓዞቹ ቅሬታቸውን ለደቡብ ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ እንደገለጹት ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ የህክምና ክትትልን ጨምሮ ለተለያዩ ማኀበራዊ ጉዳዮች አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት የየብስ ትራንስፖርት ትኬት ቆርጠው ወደ ከተማዋ ለማምራት ቢሞክሩም ህግ አስከባሪዎች ነን በሚሉ አካላት “የአዲስ አበባ መታወቂያ ካልያዛችሁ ማለፍ አትችሉም” ተብለው ተከልክለዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ የህክምና ቀጠሮ ቢኖረንም እንደ ዜጋ ሳንቆጠር ከፍተኛ መመናጨቅና ሥድብ እየደረሰብን ነው፣ ቤተሰቦቻችን ጋር የምንከውነው ልዩ ልዩ ማኀበራዊ ጉዳይ ያለ ቢሆንም በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዳንሄድ መከልከሉ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
አዲስ ስታንዳርድ ይህን አስመልክታ ከደብብ ወሎ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ሸኖ ከተማ አካባቢ እንዳይገቡ ከተከለከሉ ተጓዦች መካከል ራቢ መሃመድን [የአባት ስም ለደህንነት ሲባል የተቀየረ] ያናገረች ሲሆን ባሳለፍነው ሃምሌ ወር መጨረሻ እዚሁ ሸኖ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ እንዳትገባ መከልከሏን ታስታውሳለች። “ባለቤቴ አዲስ አበባ ከተማ ስራ በመቀየሩ የአራት አመት ህፃን ልጄን ይዤ በትራንስፖርት ከደቡብ ወሎ ኮምቦልቻ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ ሸኖ ከተማ ከመግባታችን በፊት እንዳናልፍ ተከለከልን፣” የለች ሲሆን አክላም፣ “ሁኔታው ስላላማረኝ ለጄን ይዤ ወደ መጣሁበት ተመልሼ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በጢያራ አዲስ አበባ ገብተናል” ብላለች።
የደቡብ ወሎ ዞን መንገድና ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር ይመር በበኩላቸው መምሪያው ሥምሪት የሚሰጣቸው አገር አቋራጭ አውቶቡሶች ሸኖና አካባቢው ላይ ሲደርሱ በጸጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ ክለከላ እየተደረገባቸው ስለመሆኑ ተጓዦች ቅሬታ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
አሽከርካሪዎችም ከደሴ መናኻሪያ የሚሰጣቸውን ሥምሪት ለመቀበል እየተቸገሩ መሆኑን ገልፀው የችግሩን አሳሳቢነት ለክልሉ መንግስትና ለተለያዩ ተቋማት ማሳወቃቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ም/ ኃላፊ ወይዘሮ ህሊና መብራቱ በጉዳዩ ላይ በቂ እውቅና ያላቸው መሆኑንና በርካቶች ቅሬታቸውን እያቀረቡ እንደሆነ ጠቁመው እየተፈጠረ ያለው መጉላላት የትግራይ ኃይል ከፍቶት በነበረው ጦርነት ተይዘው ከነበሩ አካባቢዎች መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶች በቡድኑ በመወሰዳቸውና ይህንን ተከትሎ በአዲስ አበባና አካባቢው ሽብር ለመፍጠር የሚያደርገውን ሙከራ ለመከላከል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አፈጻጸሙ ግን ተጠርጣሪዎችን ባለየ መልኩ ብዙሃኑን ተጓዥ ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ወጭ የዳረገ እንደሆነ ከሚደርሳቸው ቅሬታ መረዳት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች ሊያደርስ የሚችለውን ጥቃት የአማራ ክልል ህዝብም ለመመከት ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊዋ በዚህ ሳቢያ ችግር ያለበት አካል ሳይለይ በጅምላ እየደረሰ ያለው መጉላላት ተገቢ አለመሆኑንና በአስቸኳይ መስተካከል እንዳለበትም ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት አመራሮች ከአዲስ አበባ ከተማና ከሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ለመወያየትና ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጨምረው አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ከደብረ ብርሃን ተነስተው ወደ አዲስ አበባ የሚጓጓዙ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች እንደተናገሩት “አማ” ታርጋ ያለዉ ተሸከርካሪ እና የአማራ ክልል መታወቂያ የያዙ መንገደኞች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸዉ መኾኑን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ተናግረዋል፡፡ እየተፈፀመ ባለዉ እንግልት ምክንያት ሥራ ማቆማቸዉን ነዉ አሽርካሪዎች የተናገሩት፡፡ በችግሩ ምክንያት የደብረ ብርሃን ዞናል መናሃሪያ አገልግሎት መስጠት አቁሟል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ ሲሳይ ወልደአማኑኤል፤ መንገደኞችና አሽከርካሪዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱ መቆየታቸዉን አስታዉሰዉ ለችግሩ መፍትሄ ባለመቀመጡ ተሸከርካሪዎች ባሉበት እንዲቆሙ ማገደዳቸውን ገልጸዋል።
የታርጋ ቁጥራቸዉ አማራ በሆኑ ተሸከርካሪዎች ላይ ያለምንም ምክንያት የሰንዳፋና አካባቢዉ ትራፊክ ፖሊሶች እና የመንገድ ደህንነቶች እየተከሰሱ በመሆናቸዉ መስራት አለመቻላቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን የትራንስፖርት ማህበራት ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሄር ተሰማ ለኢትዮ ኤፍኤም አስረድተዋል፡፡
አሽከርካሪዎቹ ሰንዳፋ ከተማ ሲደርሱ የትራፊክ ፖሊሶች ከ1 ሺህ 5 መቶ እስከ 2 ሺህ 5 መቶ ብር የሚደርስ ቅጣት እንደሚያስከፍሏቸው ያነሱት ሰብሳቢዉ በዚህም ምክንያት መስራት እንዳልቻሉና ባለፉት ሁለት ቀናት ዉስጥ የታርጋ ቁጥራቸዉ አማራ የሚል ከ40 በላይ ተሸከርካሪዎች ያላግባብ እንደተከሰሱም ገልፀዋል፡፡ የትራፊክ ፖሊሶቹ ከክሱ በተጨማሪም አሽርካሪዎቹ ደግመዉ በዚያ መስመር እንዳይመጡ ማስፈራራታቸዉንም ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ሹፌር የተባለው ነገር እውነት መሆኑን ጠቅሶ “በዚህ ሂደት ሃገራችን ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው?” ሲል ባግራሞት ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግራል። “ቤተሰቤን፣ ልጆቼን የማስተዳድረው በሹፍርና ነው። ይህን መሰል ግፍ የሚቀጥል ከሆነ መኖር ከባድ ነው። ሃገራችንስ ወዴት እየሄደች ነው?” ብሏል።
አዲስ ስታንዳርድ ይህን ሹፌር አሁናዊ ሁኔታው ምን እንደሚመስል የጠየቀችው ሲሆን ከትናንት ነሃሴ 5 ቀን ጀምሮ የነበረው “አትገቡም ክልከላ” እንደተስተካከለ ተናግሮ በየደረጃው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ እንዲወጡ ወዳልተፈለግ ሃገራዊ ቀውስ ነገሮች እንዳያመሩ አሳስቧል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ የሆኑት ደመላሽ ያልፋል ሸኖ እና አካባቢው ያሉትን የኦሮሚያ ልዩ ሃይል እና ሚሊሻ ለችግሩ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል። እንደርሳቸው ገለፃ ደብረ ብርሃን ከተማ በአዲስ መልክ በክፍለ ከተማ ከተዋቀረች በኋላ ቀበሌዎቿን ሰሜን ሸዋ የነበሩ የድሮ ነገስታትን፣ መኳንንትን እና የሃገር ባለውለታ የነበሩ ሰዎችን ታሳቢ ያደረጉ ስያሜ መስጠቷን አውስተው ለነዋሪዎቿ እነዚህን ታሳቢ ያደረገ የቀበሌ መታወቂያ ማደሏን ተናግረዋል። “ይህን መታወቂያ ይዘን ወደ አዲስ አበባ ስንጓዝ የጠቀስኳቸው የጸጥታ አካላት ‘ነፍጠኛ’ ናችሁ አትገቡም እያሉ ሲያንገላቱን ነበር” ብለዋል። እንደ አቶ ደመላሽ ገለፃ ድርጊቱ በርሳቸው ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት እንደተከሰተ አውስተው አሁን ያለው ሁኔታ እየተስተካከለ መሆኑን ከሌሎች ሰዎች እንደሰሙና ጉዳያቸውን አዲስ አበባ ሄደው መከወን እንደሚፈልጉ ለሪፖርተራችን ተናግረዋል።
በአሽከርካሪዎች ላይ ከሚደርሰዉ ክስ በተጨማሪም የህዝብ ማመላለሻ ተሸርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ከሰንዳፋ፤ ከለገጣፎ ጭምር እንዲመለሱ መደረጉንም ሰብሳቢዉ አስታዉቀዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱን ያቋረጥነዉ አድማ ለመምታት ሳይሆን መብታችን እንዲከበር ነዉ ያሉት የማህበሩ ሰብሳቢ፣ የሚመለከታቸዉ አካላት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡አስ