ዜና: በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጠጥር ስር ማዋሉን የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ


በብሩክ አለሙ @Birukalemu21

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16/2014፦ ፋኖን ሽፋን ያደረጉ “አክራሪው” የፋኖ ቡድን አባላት ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፖሊስ ተቋማት ዕውቅና ውጪ ወጣቶችን በመመልመል፣ በድብቅ በማሰልጠንና የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ህዝቡ በፍርሀት እንዲሸበር ከማድረግ ባለፈ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን በሚዲያ እያሰራጩ እንዲሁም የንፁሃን ዜጎችን ህይወት እያጠፉ፣ እያፈናቀሉና እየዘረፉ የነበሩ ከፀጥታ አካላት ከድተው የተያዙ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸውና በቁጥጥር ስራ ሳይውሉ የቆዩ እና በግድያ ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ 5 ሺህ 804 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል ሲል የፌደራል የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ። 

ግበረ ሀይሉ ይህን ያለው በወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ሲሆን በመግለጫው አክሎም በውጭ ሀገር የሚገኙ ጽንፈኛ ሚዲዎችን በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎችን ሲያሰራጩ፣ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም በህቡዕ ሲንቀሳቀሱና በአማራ ክልል እና በፌደራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ ጥቃት ለመፈፀምና መንግስትን በኃይል ለመጣል ሲያሴሩ በነበሩ “ጽንፈኛ” የፋኖ አባላት ላይ የአማራ ክልልና የፌደራል የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በጋራ ባደረጉት የተቀናጀ ኦፕሬሽን አስራ አራቱ ከተለያዩ ሚስጥራዊ ሰነዶቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ብሏል።

በሌላ በኩል የጋራ ግብረ ኃይሉ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያው ባካሄደው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ወደ ከተማው ሰርገው በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበሩ 51 ጽንፈኛ የፋኖ አባላት፣ 174 የህወሓት አባላት፣ 98 የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት፣ በከተማው ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩ 100 ተጠርጣሪዎች እና 31 የአልሸባብና የአይ.ኤስ.ኤስ አባላትን በድምሩ 454 ተጠርጣሪዎች በመከታተል ሊያደርሱት ያሰቡትን የሽብር ጥቃት እና ትርምስ ቀድሞ በማክሸፍ በቁጥጥር ስር ማዋል ችሏል ብሏል።

በምዕራብ ወለጋ የተከሰተውን ግድያ ተከትሎ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታና ደህንነት አካላት የተውጣጣው የጋራ ግብረ-ኃይል ከሰኔ 07 እስከ ሐምሌ 07 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ዘመቻም ከ153 በላይ የሽብር ቡድኑ አባላትን በመደምሰስ፣ ከዘጠኝ መቶ በላይ ማርኮና በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ እንደሚገኝ ነው የተገለፀው፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ባካሄደው ዘመቻም መንግስት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃት ሰራዊት ይጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ የቡድንና የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያዎች፣ ብዛት ያላቸው ጥይቶችና የጥይት መጋዘኖች፣ ወታደራዊ ትጥቆችና አልባሳት፣ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶችም ተይዘዋል ብሏል፡፡

መግለጫው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ላይ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የህወሓት ሃይልን ሲፋለሙ እና ለፀጥታ አካላቱ የኋላ ደጀን ሆነው እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ የፋኖ አባላት አሁንም ይህንን መልካም ተግባር አጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቅሶ ነገር ግን ፋኖን ሽፋን በማድረግ በህቡዕ የተደራጁት አክራሪ የፋኖ አባላት ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እና በህግ-ወጥ ተኩስ ሁከት ለማስፋፋትና ክልሉ ወደ ለየለት ብጥብጥ እንዲገባ ቢሞክሩም በፀጥታ ኃይሉ እና በክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ጥረት ሙከራው ሊከሽፍ ችሏል ሲል ገልጿል።

በመጨረሻም መግለጫው እስከአሁን የተገኘው ውጤትም ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ባደረገው ቀና ትብብር መሆኑንና የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ የጀመረውን የተቀናጀ የህግ ማስከበር ዘመቻውን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለፅ ህብረተሰቡ ጥቆማውንና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.