ሰኔ13 ቀን፣2014 ዓ.ም፣አዲስአበባ፦ በምዕራብ ወለጋ ዞን ኦሮሚያ ክልል ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ 200 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ ዘገባዎች ጠቁመዋል::
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ስለነበረው ጥቃት ባወጣው መግለጫ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራው) መካከል “ከነበረው ውጊያ ጋር በተያያዘ በታጣቂው ቡድን በአካባቢው በሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” በማለት ተናግሯል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ አሳስበዋል።
በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን የተፈፀመው ግድያ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከታዩት ጥቃቶች እጅግ አስከፊው ነው። ከግጭቱ ያመለጡት የአከባቢው ነዋሪ አብዱል ሰኢድ ጣሂር ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት “230 አስከሬኖችን ቆጥሪያለሁ። ይህ በህይወታችን ካየናቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው እጅግ አስከፊ ጥቃት ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።
አብዱል ሰኢድ አክለወም “የጅምላ መቃብር ውስጥ እየቀበርናቸው ነው፣ አሁንም አስከሬን እየሰበሰብን ነው። የፌደራል ጦር ሃይሎች አሁን ደርሰዋል ነገርግን ለቀው ከወጡ ጥቃቱ ሊቀጥል ይችላሉ ብለን እንሰጋለን” ሲሉ ለዜና አውታሩ ተናግረዋል።
ለደህንነቱ በመፍራት በመጀመሪያ ስሙ ብቻ እንዲጠራ የፈለገው ሻምበል ለዚሁ ዜና አውታር እንደገለፀው የጥቃቱ ኢላማዎች ከዛሬ 30 ዓመት በፊት በአካባቢው የሰፈሩ “የአካባቢው የአማራ ማህበረሰብ” ሲሆኑ “እንደ ዶሮ እየተገደሉ ነው” በማለት ተናግሯል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባሳለፍነው ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ ታጣቂዎቹን የወቀሰ ሲሆን መንግሥት እየወሰደበት ያለውን እርምጃ መቋቋም ሲያቅተው በንጹሃን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል። በተጨማሪም በታጣቂው ቡድን ላይ የፌደራል እና የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች እርምጃውን እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አለምአቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ በተረጋገጠ የትዊተር ገፃቸው ላይ “በጊምቢ ወረዳ ቶሌ በደረሰው ግድያ እና የንብረት ውድመት የተፈፀመው የኦሮሚያ ክልል እራሱ በፈጠረው “ጋቻና ሲርና” በመባል የሚታወቅ ታጣቂ ቡድን ነው” ብለዋል።
አዲስ ስታንዳርድ በያዝነው አመት በየካቲት ወር የረዥም ጊዜ ምርመራዋ ባወጣችው ዘገባ ከተለያዩ የወለጋ ዞን አካባቢዎች የተውጣጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ማህበረሰብ አባላት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሸሽተው አዲስ አበባ ከተማ መጠለያ እየፈለጉ እንደሆነ መናገሯ ይታወሳል። ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የዚሁ ማህበረሰብ ክፍል በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን እንዲሰፍሩ መደረጉንም አዲስ ስታንዳርድ በዘገባዋ አመልክታለች።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው ምዕራብ ወለጋ ዞን በጋምቤላ ክልላዊ መንግስት አዋሳኝ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሃሙስ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ሃይሎች ከጋምቤላ ነፃ አውጭ ግንባር እና ኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ጥምር ታጣቂ ሃይሎች ጋር ባደረጉት ከባድ የተኩስ ልውውጥ በደርዘን የሚቆጠሩ ንፁሀን ዜጎች እና የጸጥታ ሃይሎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። አስ