ዜና፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በጉለሌ ክ/ከተማ በአንድ ተማሪ ላይ የድብደባ ወንጀል የፈፀሙ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገለፀ

በብሩክ አለሙ

አዲስ አበባ፡ ሰኔ 11/ 2014 ዓ.ም፡-በአዲስ አበባ ጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር ሆቴል በሚባል አካባቢ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ/ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ በትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ርቺት ተኩሶ ከት/ቤቱ አምልጦ የሄደ አንድ ተማሪን አራት የፖሊስ አባላት ተከታትለው በመያዝ የድብደባ ወንጀል እንደፈፀሙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ  አስታወቀ፡፡

ፖሊስ በደረሰው መረጃ እና ባደረገው ማጣራት ድል በር 2ኛ ደረጃ በሚባል ት/ቤት የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ  ፕሮግራም ላይ በክፍል ውስጥ በተደረገ ዝግጅት ላይ አንድ ተማሪ ርችት እንደተኮስ እና በትምህርት ቤት ውስጥ ርችት መተኮሱ ሌሎች ተማሪዎችን እንደረበሻቸው ለፖሊስ መረጃ ይደርሰዋል፡፡  

በእለቱ ድርጊቱን ፈፅሟል የተባለው ተማሪ ከት/ቤቱ ቅጥር ግቢ እንደወጣ የተነገራቸው አራት የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ክትትል በማድረግ ሰሜን ማዘጋጃ ጋበር የሚባል ሆቴል አካባቢ ተማሪውን ይዘውት ተገቢ ያልሆነ ድብደባ ፈፅመውበታል፡፡ ይህንንም የድብደባ ድርጊት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በስፋት እተሰራጨ ይገኛል፡፡

ፖሊስ መረጃው ከደረሰው በኋላ ተማሪው ላይ የድብደባ ወንጀል የፈፀሙ ተጠርጣሪ የፖሊስ አባላቱን በቁጥጥር ስር አውሎ በምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ  አስታወቋል፡፡

አክሎም የፖሊስ አባላት የህግ በላይነትን ለማስጠበቅ በሚያከናውኑት የትኛውም አይነት እንቅስቃሴ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶችን አክብሮ በማስከበር ህጋዊ አግባብ መሆን እንዳለበት  የገለፀ ሲሆን በማነኛውም ሁኔታ ውስጥ የህግ አስከባሪነት መነሻው ህግን ማክበር መሆኑን አስታውሷል፡፡ በተጨማሪም ፖሊስ የዜጎችን ህጋዊ መብት በሚፃረሩ የፖሊስ አባላት ላይ የሚወሰደውን ዕርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በማንኛውም ሁኔታ ህገወጥ ተግባራት ሲፈፀሙ ህብረተሰቡ በያገባኛል ስሜት የሚሰጠውን መረጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.