አዲስ አበባ፣ ጥር 8፣ 2015፦ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ በሆነው በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈጸምና ሃይማኖታው በዓሉን ለማወክ ሲዘጋጁ ነበሩ ያላቸውን 371 የሚሆኑ ተጠርጣሪ “የፋኖ እና የሸኔ” አባላትን እና የተደራጁ ዘራፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ቅዳሜ ጥር 6፣ 2015 ባወጣው መግለጫ መሰረት፣ ጥምር ግብረ-ኃይሉ 107 “የአክራሪ ፋኖዎች”፣ 109 “የሸኔ አባላት” እና 155 ደግሞ በህብረተሰቡ ላይ ዘረፋ ሲፈጽሙ የነበሩ ያላቸውን በድምሩ 371 ተጠርጣሪ ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል ።
“የጽንፈኛ ፋኖ ቡድን አንዳንድ የፖሊቲካ ፓርቲዎችን እንደ ሽፋን በመጠቀም የአዲስ አበባ ከተማን የሽብርና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ሐሰተኛ መታወቂያዎች በመያዝ በከተማዋ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ዝግጅት እያደረጉ ባለበት ወቅት እጅ ከፍንጅ ጠይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡
መግለጫው አያይዞም በትምህርት ቤቶች የተነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን አቅጣጫ በማሳት ለእኩይ ዓላማ በመጠቀም የከተማውን ህዝብ በብሄር ለማጋጨት እና ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር እንዲሁም የተለያዩ በትጥቅ የታገዘ ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 109 “የፅንፈኛው ፋኖ ቡድን አባላት ከሚጠቀሙባቸው የጦር መሣሪያዎችና ከተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት” ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አትቷል።
መግለጫው አያይዞም “በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው የተቀናጀ ህጋዊ እርምጃ ተሸሽገው አዲስ አበባ ከተማ በመግባት የሽብር ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 107 የ ‘አሸባሪው ሸኔ’ ቡድን አባላት ለጥቃት ከሚጠቀሙባቸው የጦር መሣሪያዎችና ከተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት ጋር በቁጥጥር ሥር ” እንደዋሉ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ተደራጅተው በጦር መሣሪያና በድምጽ አልባ የስለት መሣሪያዎች በመታገዝ በሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ዘረፋ በመፈፀም ኅብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የጣሉና ያማረሩ 155 ተጠርጣሪዎች ከዘረፏቸው እና ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ መሣሪያዎች ጋር ከነ-ግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ግብረ-ኃይሉ ገልጿል።
እንደ ግብረ-ኃይሉ መግለጫ የአዲስ አበባ ከተማን እና ዙሪያውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ግብረ-ኃይሉ ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ በአካሄደው ኦፕሬሽን 371 ተጠርጣሪዎችን ለሽብር ካዘጋጁት የጦር መሣሪያ እና ከዘረፏቸው ንብረቶች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን ነው።
“ከተጠርጣሪዎቹም ሚስጥራዊ ሰነዶች፣ ሐሰተኛ መታወቂያዎች፣ የክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች፣ ቦንቦች፣ ሽጉጦች፣ በርካታ ጥይቶችና የተለያዩ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት እንዲሁም ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያ የሚጠቀሙበት ገንዘብ፣ የዘረፉት ተሽከርካሪዎችና የተለያዩ ንብረቶች በኤግዚቢትነት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም” የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል፡፡
የጋራ ግብረ-ኃይል አያይዞም የጥምቀት በዓል በተለይ በአዲስ አበባ በርከት ያለ ህዝብ እና ከተለያዩ ዓለም ሀገራት የሚመጡ ቱሪስቶች የሚታደሙበት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች እና ከተማው ነዋሪዎች በተለየ ሁኔታ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተቀራርበው እንዲሠሩ ጥሪውን አቅርቧል።
መላው ሕዝብ ፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚያደርሱትን ጥፋት በውል ተገንዝቦ እንደተለመደው ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ሰላሙን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች እንዲሁም በስልክ ቁጥር 011-1-11-01-11፣ 251115-52-63-03፣ 251115-52-40-77፣ 251115-54-36-78 እና 251115-54-36-81 ጥቆማ መስጠት እንደሚቻል የጋራ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል፡፡
ባለፈው አመት ሀምሌ ወር የጋራ ግብረ ሃይሉ ከ “አልሸባብ”፣ “አይሲስ”፣ “ሸኔ” ፣ “የህወሓት ጁንታ”፣ እና “ጽንፈኛ ፋኖ” ጋር ግንኙነት ያላቸው ሃይሎች በዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ እና አካባቢዋ ላይ ሊያደርሱ ያሰቡትን “የሽብር ጥቃት” ጨምሮ ከፍተኛ የደህንነት ስጋትን መከላከል ተችሏል ብሏል።
በዚህም መሠረት 554 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የገለፀ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 51ዱ የ “ጽንፈኛ ፋኖ”፣ 174 “የሕወሃት ጁንታ” ቡድን፣ 98 የ “ሸኔ ቡድን” አባላት፣ 100 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በከተማዋ ሁከት ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ እና 31 የአል-ሸባብ አባላት መሆናቸውን ገልጾ ነበር ። አስ