ዜና፡ የድሬዳዋ አስተዳደር ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ወይም ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወደ አንዱ እንዲጠቃለል ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8/2015 ዓ.ም፡- የድሬዳዋ አስተዳደር ራሱን የቻለ ክልላዊ መንግሥት እንዲሆን ወይም ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ወደ አንዱ እንዲጠቃለል ሪፈረንደም እንዲካሄድ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ቀረበ፡፡

ጥያቄው የድሬዳዋ አስተዳደር እያጋጠመው ካለው የበጀት እጥረት፣ ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍልና በዕድገት የመቀጨጭ ችግሮችን ለመቅረፍ የማይቻል ከሆነ፣ መፍትሔ ያስፈልጋል በሚል ለሁለቱ ምክር ቤቶች ቀርቧል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

ጥያቄው የቀረበው፣ ረቡዕ ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ባካሄዱበት ጊዜ  ሲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገርና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ጉዳዩ በሌላ ጊዜ የሚታይ መሆኑን በመግለጽ፣ በዕለቱ በነበረው የንብረት ግብር ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲተኮር ጠይቀዋል፡፡

የድሬ ዳዋ ተወካይ አቶ አብዱልጀዋድ መሐመድ ለሪፖርተር እንደተናገሩት “ድሬዳዋ በቻርተር በቀጥታ በፌዴራል መንግሥት ሥር መግባቷ በእጅጉ ጎድቷታል፡፡ ሌሎች ክልሎች ያመነጩትን ገቢ በቀመር ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሲካፈሉ፣ ከድሬዳዋ የሚመነጨው ግብር ግን በቀጥታ ለፌዴራል መንግሥት ገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ድሬዳዋ ከምታመነጨው ትልቅ ገቢ በፍትሐዊነት ተካፋይና ተጠቃሚ እንድትሆን የግድ የክልል ጥያቄ ጉዳይ መፍትሔ እንዲበጅለት እየተጠየቀ ነው” ብለዋል፡፡

አክለውም ከድሬ ዳዋ የሚገኘው ገቢ በሙሉ ወደ ፌዴራል ይሄዳል፡፡ በቻርተር መተዳደር ከጀመረች ወዲህ ዕድገቷ ወደኋላ ተመልሷል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ድሬዳዋ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በቻርተር በቀጥታ በፌዴራል መንግሥት ሥር የምትተዳደር ሲሆን፣ ይህም ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሚቀርበውን የይገባኛል ጥያቄ ለማለዘብ፣ ኢሕአዴግ ያመጣው የአስተዳደር አማራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ድሬዳዋን በየአራት ዓመቱ በመቀያየር በተራ ያስተዳድራሉ፡፡ ለድሬዳዋ የሚደርሰው የተወሰነ የድጎማ በጀትም በክልል መንግሥታቱ መልካም ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የድሬዳዋ ባለሥልጣናት ይገልፃሉ ሲል ሪፖርተር ዘግቧል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.