ዜና፦የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር እና ለትምህርት ቤቶች የምግብ ፕሮግራም የሚያግዝ 33 ሚሊየን ዩሮ ለገሰ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/ 2015 ዓ.ም፡- የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ትምህርትን ለማስጀመር እንዲሁም ለተማሪዎች ምገባ የሚያግዝ 33 ሚሊዮን ዩሮ በኣለም አቀፉ የህፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) እና በዓለም ምግብ ፕሮገራም (WFP) በኩል ድጋፍ ሰጠ።

የትምህርት አገልግሎትን ወደነበረበት ለመመለስ እና የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ 1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር (33 ሚሊየን ዩሮ) በዐዓለም ህፃናት መርጃ ድርጅትና በዓለም ምግብ ፕሮገራም ትብብር የሚፈጸም መሆኑን የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የድጋፊ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ህጻናት ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ማድረግ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው በዚህ ድጋፍ 80,000 የሚጠጉ ህጻናት ተጠቃሚዎች ይሆናሉ እና 60 ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ስራም ይከናወናል።

የተደረገው ድጋፍ 50,000 ህጻናት በግጭት በተከሰተ ሰሜናዊ ኢትዮጵያ የተመጣጠነ የትምህርት ቤት ምግብ በኣለም ምግብ ፕሮግራም በኩል እንዲያገኙ ያስችላል።

የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ እንደሚሉት በየትኛውም ጦርነት ህፃናት ሰለባዎች በመሆናቸውና ለበለጠ ስቃይ ስለሚዳረጉ በዚህ አካባቢ የሚገኙ ህፃናትም ሕይወታቸው ተረብሿል ትምህርታቸውም ተቋርጧል ይህንን ለማስተካከል ድጋፉ ያግዛል።

“በመላ ሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሆነዋል” ይላሉ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ። 

የሰላም መንገድን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ህጻናትን ወደ ትምህትት እንዲመለሱ ለመርዳት ቁርጠኛ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።

መግለጫው “የልጆች ጥራት ያለው ትምህርት የማግኘት አስተማማኝነት ለአገሪቱ የወደፊት ሁኔታ ወሳኝ ነው” ሲል አፅንዖት ሰጥቷል።

በመግለጫው መሰረት በግጭት በተጎዱ 10 ክልሎች ከ8,500 በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል ተጎድተዋል ወይም በጠቅላላ ወድመዋል።  በሰሜን ኢትዮጵያ ብቻ ደግሞ ከ1,500 በላይ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት የማይሰጡ ሆነዋል።
“በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱ ህፃናትን በተለይም ሴት ልጆችን በትምህርት ቤት ለማቆየት የአውሮፓ ህብረት ለዓለም ምግብ ፕሮገራም የትምህርት ቤት ምገባ በወቅቱ ለማቅረብ አጋዠ ድጋፍ ነው ” ሲሉ የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እና ተወካይ ክላውድ ጂቢዳር ተናግረዋል።

እንደ ተወካዩ ገለጻ ህጻናት አጋጥሟቸው ያለውን ወቅታዊ ረሃብ ለማስታገስና በቀጣይም አልሚ ምግቦችን ለማቅረብ እና በትምህርት ቤት ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት በማሻሻል የሰው ሀብት ልማት ላይ ውጤታማ ለመሆን ያስችላል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.