ዜና፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታወቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህዳር 06 በፓርላማ ። የምስል ክሬዲት፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

አዲስ አበባ፣ህዳር 08/2015 ዓ.ም. ፦መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታወቁ፡፡

የተቋቋመው ኮሚቴ ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ እነርሱም፡- አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ፣ አቶ ተክለ ወልድ አጥና፣ አቶ ሰሎሞን ሶቃ፣ አቶ ደበሌ ቃበታ፣ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና አቶ አብዱሃሚድ መሃመድ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚንስቴሩ የኮሚቴውን መቋቋም ይፋ ባደረጉበት መግለጫ “ሙስና አገርን የሚበላ ነቀዝ ነው፡፡ የአገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው። ዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሃብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ፤ ከነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዛት ያላቸው ዜጎች መሰለፍ ሲጀምሩ ሙስና የተባለው ነቀዝ አገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል” ብለዋል፡፡

መግለጫው መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግስት ተቋማት ሰራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ገልፆ ነገር ግን ሙስና በባሕሪው በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን የሚካሄድ በመሆኑ በመንግሥት ጥናት የተደረሰባቸው አካላትን ብቻ ለሕግ በማቅረብ የሚፈታ አይደለም ብሏል፡፡ አክሎም ሙስናን ከሥር ከመሠረቱ ለመንቀል እንዲቻል ከሕግና ከአሠራር ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ የሙስና ተዋንያን ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ ርምጃ ያስፈልጋል ሲል ገልጧል፡፡

ሀገራችን ያጋጠማትን ጦርነትና ኮሮናን የመሳሰሉ ወረርሽኞች የመንግሥትን ትኩረት ወስደዋል ብለው ያሰቡ ሙሰኞች፣ በየቦታው ተሠግሥገውና ኔትወርክ ዘርግተው፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሠሩ መሆናቸውን የጥናት ሪፖርት ያሳያል ብሏል መግለጫው፡፡

ብሄራዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና የእንቅስቃሴው ውጤት በየጊዜው ለህዝብ ይፋ ይደረጋል የተባለ ሲሆን የየክልሉ ርእሳነ መስተዳድሮች በየደረጃው የሚሠሩ ክልላዊ ኮሚቴዎችን በቅርቡ ያቋቁማሉ።

ህብረተሰቡም የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ ከቂምና በቀል ነጻ በሆነ መንገድ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል፡፡፡ አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.