ዜና፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድረገው ሾሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2015 ዓ.ም፡– የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት አስታወቀ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ ቤት  ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢፌዴሪ የፌዴሬሸን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2/ለ/ መሠረት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፣ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግስት እና በህወሓት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እና ግጭትን ለማስቆም በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምት አንቀጽ (10) መሰረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም አስፈልጓል ሲል ገልጧል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት መጋቢት 9 ቀን 2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን ማጽደቁ ተመላክቷል ያለው መግለጫው በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሰረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አድርገው መሾማቸውን አስታውቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥ እና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈጻሚ አካል የመምራት እና የማስተባበር ሃላፊነት እንደተጣለባቸውም መግለጫው አክሎ ገልጧል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባውን ያካሄደው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ማዕከላዊ ኮምቴ፣ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባል የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን የክልሉ ግዜያዊ አስተዳደር እንዲመሩ መምረጣቸውን ተከትሎ ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ ከ41 የማዕከላዊ ኮምቴ አባላት 18 የድምጽ ብልጫ በማግኘታቸው ነው የጊዚያው አስተዳደሩን እንዲመሩ የተመረጡት፡፡

የጠቅላይ ሚንስቴሩ መፈግለጫ የወጣው በትላንትናው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ከሽብርተኝነት ዝርዝር ማንሳቱ ተከትሎ ነው፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.