ዜና፡ የትግራይ የጦር ጉዳተኞች በመቀሌ በሰላማዊ ሰልፍ ያቀረቡት ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ዕጩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ቃል መግባታቸው ተገለጸ

photo from social media

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13/ 2015 ዓ.ም – አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ዕጩ ፕሬዝዳንት የትግራይ ሰራዊት የጦር ጉዳተኞች የጠየቁት ጥያቄ አግባብነት ያለው የመብት ጥያቄ በመሆኑ ትኩረት እንደሚሰጠው አስታወቁ። በትላንትናው እለት መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የትግራይ የጦር ጉዳተኞች ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወቃል። የክልሉ ህዝብ ባለፉት ሁለት አመታት ከፌደራል መንግስቱ ጋር ባካሄደው ጦርነት ለአካል ጉዳት የተዳረጉ እና የቆሰሉ ተዋጊዎች በመቀለ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ ተርበናል የሚል መፎክሮችን ሲያሰሙ ተደምጠዋል። ምግብ እና መድሃኒት እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ አካል ጉዳተኞቹ የጠየቁት ወሳኝ ጥያቄ የምግብ፣ ንጽህና እና የህክምና አቅርቦት መሆናቸውን አስታውቀው ጉዳዩ ሊመረመር እና አትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በመቀለ ከተማ ኩይሃ መለስ ካምፓስ እና ደጀን ሆስፒታል የሰሜን እዝ ካምፕ በሚባሉ ሁለት ወታደራዊ ሰፈሮች ተጠልለው የሚገኙት የጦር ጉዳተኞቹ በተጨማሪም በጦርነቱ ህይወታቸውን ለገበሩ ታጋይ ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈላቸው እና ክብር እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።  

በሰልፉ ተካፋይ የነበረው እና ከጦርነቱ በፊት በአዲግራት ዩኒቨርስቲ መምህር የነበረው መድሃኒየ ህሉፍ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀው ‘’የቀኝ እጄ አይሰራም፣ መጻፍም ሆነ መብላት አልችልም፣ የህክምና እርዳታ ለማግኘት ሁለት ወራት ጠብቂያለሁ፣ የተሻለ ህክምና ለማግኘት በርካታ ግዜያት ጠይቂያለሁ፣ ምንም ምላሽ አልተሰጠኝም፣ ቤተሰቦቼ ናቸው ያሳከሙኝ’’ ሲል ገልጿል።  

‘’ምንም የቤተሰብ እርዳታ ማግኘት የማይችሉስ? በመድሃኒት እጥረት ቁስላቸው የተባባሰባቸው አሉ፣ በህግምና እርዳታ እጥረት እጃቸው እና እግራቸው የተቆረጠ ብዙ ወጣቶች አሉ’’ ሲል የገለጸው መድሃኒየ በጦርነቱ ለተሳተፉ ወታደሮች ተብሎ የመጣ መድሃኒት በግል ፋርማሲዎች በመሸጥ ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

የታገልነው ለመብታች፣ ለዲሞክራሲ እና ለህዝባችን በመሆኑ ክብር ሊሰጠን ይገባል ሲል የተናገረው መድሃኒየ የህክምና እርዳታ እና ምግብ ሊቀርብልን ይገባል፤ እንደእውነቱ ከሆነ ይህ እንደ ጉዳይ ሊቆጠር ባልተገባው ነበር፤ ያሳፍራል ሲል ገልጿል።

ወደ ቀድሞ ስራየመመለስ እፈልጋለሁ፤ ለዚህም የተሻለ ምግብ እና ህክምና ያስፈልግኛ ሲል ገልጾ ነገር ግን ይሄን ማቅረብ ትተው እያስራቡን ይገኛሉ ሲል ተችቷል።

ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ ከመቀለ እንዳስታወቁት በክልሉ የሚገኙ አድማ ብተና የጸጥታ ሀይሎች እና ታጣቂዎች የአካል ጉዳተኞቹ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያካሂዱ ሊያግዷቸው ሞክረው እንነበር እና አስለቃሽ ጋዝ እንደተኮሱባቸው ገልጸዋል። አቶ ጌታቸው ከአካል ጉዳተኞቹ ጋር ግልጽ ውይይት ማካሄዳቸውን እና ጉዳያቸውን ትኩረት ሰጥተው በማየት ምላሽ ለመስጠት ቃል እንደገቡላቸው ምንጮቻችን አክለዋል።

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.