አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2015፡- በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተወካዮች መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመውን የግጭት ማቆም ስምምነት ተከትሎ በክልሉ ርዕሰ መዲና መቀሌ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
አዲስ ስታንዳርድ ከመቀሌ እንዳገኘዉ መረጃ እንደ ጤፍ፣ ስንዴ እና የስንዴ ዱቄት ያሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ድንገተኛ የዋጋ ቅናሽ አሳይቷል።
በሰላም ስምምነቱ ምክንያት የምግብ አቅርቦት ሊጨምር እና የዋጋ ቅናሽ ሊኖር ይችላል በሚል ስጋት ነጋዴዎች “ያጠራቀሙትን ሁሉ እየሸጡ ነው” ይላል የአዲስ ስታንዳርድ የመረጃ ምንጭ ።
ከወራት በፊት በ14,000 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ጤፍ አሁን ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በግማሽ ገደማ ቀንሶ በ8000 ብር እየተሸጠ መሆኑን ቢቢሲ ትግርኛ ዘግቧል።
የስንዴ ዋጋም ከ9000 ብር ወደ 3000 ብር የቀነሰ ሲሆን ስኳር፣ ዘይትና በርባሬ የዋጋ ቅናሽ ካሳዩ ሌሎች ምርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በትግራይ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን ይህም በዋነኛነት የባንክ አገልግሎት ከሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ጋር በመቋረጡ ምክንያት በተፈጠረ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደሆነ ይነገራል።
በክልሉ ምንም አይነት የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገድ ስላልነበር ደሞዝ ጨምሮ የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም ከባድ ነበር። ከትግራይ ውጭ ያለ አንድ ሰው በግለሰቦች አማካኝነት ለቤተሰብቦቹ ገንዘብ ለመላክ 40% የአገልግሎት ክፍያ ይጠየቅም ነበር።
የፌደራል መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል አስከፊ ጉዳት ያደረሰዉን ጦርነት ለማስቆም ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ሃይሎች ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል። ይህም ከአመት በላይ ተለያይተው የነበሩ የትግራይ ቤተሰቦች የመገናኘት ተስፋን እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል። አስ