በብሩክ አለሙ @Birukalemu21
አዲስ አበባ፣ የካቲት 24/2015 ዓ.ም፡- የጉራጌ ዞን የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ መኑር ረሺድ፣ የዞኑ ምክር ቤት ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩት ወ/ሮ ጠጄ ደመቀ፣ የከተማ ንግድና ኢንተርፕራይዝ ኃላፊ አቶ አስራት ታደለ፣ የወልቂጤ ከተማ የገቢዎች ኃላፊ አቶ ሰፋ ጀማል፣ ወልቂጤ ከተማ የአዲስ ክፍለ ከተማ የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ፍቃደ፣ የክልል የኢንደስትሪ ማዕከል ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አዛታ፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ሪጂስተራር ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ምኑታ፣ በደቡብ ክልል ልዩ ሃይልና በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የተከማዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለፁ፡፡
በተማሳሳይ መልኩ የጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ በየነ ወልዴና ዘርማው ይትባረክ እንዲሁም ጠበቃና የህግ አማካሪ ጀምበር አብዶ በአዲስ አበባ መታሰራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለሱ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ በአመራር ላይ ካሉት በተጨማሪም ከ15 በላይ የማህበረሰብ አንቂዎችና ወጣቶች እስር ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው “ለእስር የተዳረጉት ለጉራጌ ዞን ማህበረሰብ በመንቆርቆር በሰላማዊ መንገድ በመታገላቸው ነው” ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እስሩ ከማክሰኞ እለት ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ነዋሪው የፀጥታ አካላቱ ያለ ምንም የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ከለሊቱ 9፡00 ሰዓት ላይ በር እየሰበሩ በርካታ ሰዎችን ማሰራቸውንም አስረድተዋል፡፡
“የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሀይል ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በመጣመር ተልኮአቸውን እያከናወኑ ነው፡፡ ልዩ ሃይሉን የፌዴራል ደምብ ልብስ በማልበስ አፈና እያካሄደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰዒድ (ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ) እንደሚናገሩት አንዳንድ የታሰሩት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ በፀጥታ ሀይሎች እንደተፈፀመባቸው ገልፀው በአሁኑ ሰዓትም ተጨማሪ ሰዎችን ለማሰር ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለእስር ከተዳረጉት መካከል የክላስተር አደረጃጀትን ውድቅ በማድረጋቸው ከሃፊነት እንዲነሱ የተደረጉት የጉራጌ ዞን የምክር ቤት ቋሚ ሰብሳቢ የነበሩት ወ/ሮ ጠጄ ደመቀ የሰባት ወር ነበሰ ጡር ናቸው ያሉት አቶ ሰኢድ ያለ አግባብ መታሰራቸውን ገልፀዋል፡፡
አንድም ጠንካራ የመንግስት ተወካይ መጥቶ በዞኑ ላይ ለአራት አመታት የዘለቀውን ችግር ለመፍታት ጥረት ያደረገ አካል የለም የሚሉት አቶ ሰኢድ በዚህም የተነሳ ማህበረሰቡ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ነው ያለው ብለዋል፡፡ አክለውም መንግስት በመህበረሰቡ ላይ ማስፈራራት እየፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው ገዢው ፓርቲ ወደ በሰላማዊ መንገድ ወደ ድርድር ቢመጣ መልካም ነው ብለዋል፡፡
የጉራጌ ማህበረሰብ በክላስትር የመደራጀት ውሳኔን ውድቅ በማድረግ ዞኑ ወደ ክልልነት እንዲያድግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ የዞኑ ምክር ቤትም የክላስተር አደረጃጀትን ውድቅ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ በቅርቡም ለአራተኛ ጊዜ ስራ አማቆም አድማ በወልቂጤ ከተማ እና በአንዳንድ የዞኑ ወረዳዎች ላይ ተደርጓል፡፡
በዚህ ንቅናቄ ላይ የተሳተፉ አመራሮች እና 100 የሚሆኑ ወጣቶች መታሰራቸውም ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የጉራጌ ዞን በተደረጃ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የክልሉ ልዩ ሃይል፣ የፌድራል ፖሊስ እና ሌሎችም የፀጥታ አካላትን ጨምሮ በቅንጅትና በተደራጀ መንገድ በዞኑ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውነን የፀጥታ ችግር እንዲፈታ መወሰኑን የደቡብ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ በእለቱ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡አስ