አዲስ አበባ፣ ጥር 4/ 2015 ዓ.ም፡- የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪ ኮሎናን እና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ባኤርቦክ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በዛሬው እለት አዲስ አበበ ገብተዋል፡፡ ጉብኝታቸውም ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና የአውሮፓ ህብረት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ሀገሪቱን እና ህዝቦቿን እንዴት መደገፍ እንደሚችሉ መገንዘብ ስለፈለጉ ነው ተብሏል፡፡
ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ይወያያሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ያደረግነው ጥልቅ እና ፍሬያማ ውይይታችን ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን ጋር ያላትን ጠንካራ እና የቆየ ግንኙነትን የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል። ቀደም ሲል ሁለቱም ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
የጀርመን ፕሬስ ድርጅት ዲፒኤ,የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባኤርቦክ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው በሰሜን ኢትዮጵያን ለሁለት አመት የዘለቀውን አውዳሚ ጦርነትን ለመቋጨት በፌዴራል መንግስት እና በትግራይ ክልል ባለስልጣናት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ አውሮፓ አሁን “ፊቷን በፍጥነት ማሳየቷ አስፈላጊ ነው” ብሏል።
“ሌላው የውይይቱ ትኩረት የሰብአዊ መብቶች ጥያቄ ይሆናል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባዎች፣ በግጭቱ ወቅት በሁሉም አካላት የከፋ የሰብአዊ መብት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ወንጀሎችን እና ወንጀለኞችን መርምሮ ለህግ የሚያቀርብ የሽግግር የፍትህ አሰራር ለመዘርጋት እየሰራ ነው። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ለአለም አቀፉ ኮሚቴ ባለሙያዎች ወንጀሎቹን እንዲያጣራ ትእዛዝ ሰጥቷል” ተብሏል።
ባኤርቦክ እና ኮሎና ዛሬ ከሰአት በኋላ ከዩክሬን የተበረከው እህል የሚከማችበትን በአዳማ ከተማ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ማቀናበበሪያን እንዲጎበኙ የዲፒኤ ዘገባ ያስረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ትልቁ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ማከማቻ ሲሆን 218,000 ቶን የመያዝ አቅም አለው፡፡
ዩክሬን ለኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ያበረከተችውን 50,000 ሺህ ቶን ስንዴን ጀርመን እና ፈረንሳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም የምግብ ፕሮግራም በኩል እያንዳንዳቸው 14 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ወጪ በማውጣት የማጓጓዝና የማከፋፈል ድጋፍ አድረገዋል፡፡ ጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭ የሸፈነች ሲሆን፣ ፈረንሳይ ደግሞ ወደ ሶማሊያ ለማድረስ የሚያስፈልገውን ወጭ ሸፍናለች፡፡አስ