ዜና፡ የኢ.ኦ.ተ.ቤ.ክ ቅዱስ ሲኖዶስ በትግራይ ክልል የተመሰረተው አደረጃጃት ሕገወጥ ነው ሲል ገለጸ፤ የቤተ ክርስቲያኗን ተቋማዊ አንድነት በማስጠበቁ ረገድ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሚና እንዲጫወት ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16/ 2015 ዓ.ም፡– የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ትልንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የሚገኙ የእምነቱ አባቶች የቤተ ክርስቲያናችንን ጸንቶ የቆየ ተቋማዊ አንድነትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀትን በሚንድ መልኩ “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጽ/ቤት የሚል አዲስ ሕገወጥ ክልላዊ መዋቅር መፍጠራቸውን ህገወጥ ተግባር ነው ሲል አስታወቀ

መግለጫው በተጨማሪም የቤተክርስቲያኗን ህግ በመጣስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ውጭና ያለቅዱስ ፓትርያርኩ ፊርማ የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖናዊና አስተዳደራዊ አሠራርን በጣሰ ሁኔታ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሊቃነ ጳጳሳት ተመድበው በሚሠሩባቸው የውጭ ዓለማት አህጉረ ስብከት ላይ ሊቃነ ጳጳሳት ከቀኖና ውጭ ራሳቸውን በራሳቸው መመደባቸው እንዳሳዘነው አመላክቷል።

የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ መግለጫውን ያወጣው ከቀናት በፊት የትግራይ ክልል የሚገኙ የእምነቷ አባቶች “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” በሚል በውጭ ሀገራት ለሚገኙ አብያተ ክርስትያናት የሚያገለግሉ ጳጳሳትን በመሾማቸው ነው።

ሲኖዶሱ በመግለጫው ‘’የእምነትና የታሪክ መሠረት በሆነው በታላቁ የትግራይ አህጉረ ስብከት እንዲህ ዓይነት መዋቅርን የሚንድና ቤተ ክርስቲያናችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ በዓለም መላውን የእምነቱን ተከታዮች የሚያሳዝን አድራጐት ለታሪካዊ ለትግራይ ሕዝብና ሊቃውንት የማይመጥን አድራጎት ነው’’ ሲለ አስታውቋል።

በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት በሀገሪቱ ካስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኗ ተቋማዊ መዋቅር ላይ አደጋ መፍጠሩን ቤተክርስቲያኗ በመግለጫው አስታውቃለች።

በጦርነቱ ሳቢያ በቤተክርስቲያኗ የበላይ መዋቅርና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት መካከል አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ግንኙነት መቋረጡን ያወሳው መግለጫው በዚህም ሳቢያ  በጦርነቱ ምክንያት ሁሉም የባንክ ተቋማት ሥራቸውን በማቆማቸው በየጊዜው እንደሌሎች አህጉረ ስብከት ለትግራይ አህጉረ ስብከት ይላክ የነበረው በጀት መላክ አለመቻሉን ጠቁማለች።

በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት በጀት እንዳይላክ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነ አንድም ውሳኔ የሌለና በተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የባንክ አገልግሎት በመቆሙ የተከሰተ የግንኙነት መቋረጥ መሆኑ ታውቆ በጀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ከአህጉረ ስብከት ጋር በመነጋገር ለመላክ ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች።

በትግራይ አባቶች በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የጦርነቱ ደጋፊ በሚያስመስል መልኩ የተሰጠው መግለጫ ተቀባይነት የሌለውና ቤተ ክርስቲያኗን የማይገልጽ ነው ሲል ሶኖዶሱ በመግለጫው ተችቷል፡፡

በክልሉ ያለው አጠቃላይ መዋቅራዊ ችግሮችን በሚመለከትና አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የተከሰቱትን ችግሮች ተወያይቶ ለመወሰን መጋቢት 21 ቀን 2015ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ መጠራቱን ያስታወቀው ዘገባው በክልሉ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመድበው በመሥራት ላይ የሚገኙ ሊቃነጳጳሳት በጥሪው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስቱም በክልሉ ተፈጥሮ የቆየው ችግር በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፈታቱ ቤተ ክርስቲያኗ የተሰማትን ደስታ ሲኖዶሱ በመግለጫው አስቀምጧል። ሲኖዶሱ በመግለጫው ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባቀረበው ጥሪ በክልሉ በሚገኙ የቤተክርስቲያኗ አባቶች እና በቤተክርስቲያኗ መካከል የተፈጠረውን ተቋማዊ አንድነትን የሚጥስ ተግባር እንዲቆም የበኩሉን ሚና እንዲጫወት አሳስባለች።

ለፌደራል መንግስቱም ሲኖዶሱ በመግለጫው ባስተላለፈው ጥሪ እንደአሁን ቀደሙ በሲኖዶሳዊ አንድነት ላይና በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ የተጋረጠው ችግር ልዩ ትኩረት በመስተጠና የበኩሉን ሚና በመጫወት የቤተ ክርስቲያናችንን ሲኖዶሳዊ አንድንትና ነባር መዋቅራዊ አደረጃጀት ጸንቶ እንዲኖር አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቃለች።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.