ዜና፡ የሀገራዊ የፍትህ ስርአቱ በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዳኘት የተሟላ ቁመና ይኖረዋል ብለን አናምንም ሲሉ የትግራይ ግዝያዊ ኣስተዳደር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/ 2015 . የሀገራዊ የፍትህ ስርአቱ በትግራይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ለመዳኘት የተሟላ ቁመና ይኖረዋል ብለን አናምንም ሲሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንቱ ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ  ፍትህ መረጋገጥ እንዳለበት ጠቅሰው የፖለቲካ መፍትሄዎች እና ሰላም በተሟላ መልኩ በዘላቂነት ሊረጋገጥ የሚችለው የፍትህ ጥያቄዎች ሲመለሱ ነው ብለዋል። አክለውም በሀገር ደረጃ የቱንም ያክል የተሟላ የፍትህ ስርአት ብንዘረጋ በትግራይ ጦርነት የተፈጸሙ ወንጀሎችን በተሟላ ደረጃ ያረጋግጣል ብለው እንደማያምኑ ያስታወቁት አቶ ጌታቸው “ለምሳሌ ለመጥቀስ ያክል የኤርትራ ሰራዊት የፈጸማቸውን ግፎች በየትኛው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ነው መዳኘት የሚቻለው ሲሉ”ጠይቀዋል። የኤርትራ ሰራዊት የፈጸማቸው ግፎች ዝም ብሎ ተራ በጦርነት ምክንያት የተፈጸሙ አይደሉም፤ሆን ተብለው ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋትና ለማንበርከክ እና ተቋማትን እንደ ተቋማት ለማጥፋት ተብሎ የተደረጉ ስራዎች አሉ ሲሉ ኮንነዋል።

በሀገር ደረጃ የሽግግር ፍትህ እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም ነገር ግን የተፈለገውን ያክል የተሟላ የፍትህ ስርአት ብንዘረጋ በትግራይ የተፈጸሙ በደሎች በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና ይኖረዋል ብለን አናምንም ብለዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በይፋ ስራ ጀምሯል ማለት እንደሚቻል ያስታወቁት የትግራይ ግዝያዊ ኣስተዳደር ፕሬዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የመጀመሪያ ስራዎች መካከል ዋነኛው ከቀያቸው የተፈናቀሉ እንዲመለሱ ማድረግ እና ማህበራዊ ግልጋሎቶችን ማስጀመር ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

በርካታ የትግራይ ግዛቶች አሁንም በኤርትራ እና በአማራ ታጣቂዎች በጉልበት ተይዘዋል ሲሉ የተደመጡት አቶ ጌታቸው አሁንም በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ግፍ በመፈጸም ላይ ነው፤ ይህንን የማስቆም ሃላፊነት የፌደራል መንግስቱ ግዴታ ነው ብለን እናምናለን ብለዋል። እስካሁን ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ከመመለስ አንጻር መሰራት ያለባቸው ቀሪ በርካታ ስራዎች አሉ ያሉት ፕሬዝዳንቱ ህዝቡን ወደ ተረጋጋ ኑሮ ለመመለስ የሚያስችሉ ማህበራዊ ግልጋሎቶችን በተሟላ መልኩ ከማምጣት አንጻር በጣም ሰፋፊ ጉድለቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ፖለቲካ ውይይቶችን ለማካሄድ የጊዜያዊ አስተዳደሩ በመመስረቱ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ያመላከቱት አቶ ጌታቸው ቀጣይ ግንኙነቶች በፖለቲካዊ ውይይት ይፈታሉ ተብለው የተቀመጡ በርካታ ርዕሶችንም በተሟላ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ቁመና ከመፍጠር አንጻር ትልቅ ሂደት ተከናውኗል ብለዋል።

ግዜያዊ አስተዳደሩ እስኪመሰረት ድረስ ሊቆዩ የማይገባቸው ተግባራት በፌደራል መንግስቱ በኩል አለመፈጸማቸውን ያስታወቁት አቶ ጌታቸው ረዳ  በህገመንግስቱ መሰረት መፈታት የነበረባቸው ጉዳዮች የኤርትራ ሰራዊት መውጣት፣ ሌሎች ታጣቂዎች መውጣት ጋር በተያያዘ በጎ ጅምሮች ያሉ ቢሆንም መጠናቀቅ ያለባቸው ጉዳዮች አሉ በሂደት መልካም ግንኙነቱ እየተጠናከረ በሄደ ቁጥር ሰላማዊ በሆነ አገባብ ህገመንግስታዊ በሆነ አገባብ ከስሜት በጸዳ መልኩ ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮች መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የምንቀጥልባቸው ይሆናል ብለዋል።

ከጎረቤቶቻችን ጋር ብዙ ተዳምተናል፣ ይሄ መቀጠል አይችልም፤ ከስሜት በጸዳ መልኩ በሰላማዊ መንገድ በህጋዊ እና በህገመንግስታዊ መንገድ እየከበደንም ቢሆን መልመዱ የሚያዋጣነው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

አሁንም የሚታዩት ችግሮች በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እንደተጠበቀ ሁኖ በሀገር ደረጃ የሚታየው የሰላም ጭላንጭል አደብዝዞ ወደ ለየለት ቁሩቁስ ለመግባት ከመፍጠር አንጻር ያለው ትርጉም ከፍተኛ በመሆኑ በፌደራል መንግስትም፣ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም ዘንድ እና ከምንም ነገር በላይ ወንድም በሆነው የአማራ ህዝብ ዘንድ ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት እልባት ሊያገኝ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። ግጭቱን ያስቆምነው ተመልሰን ወደ ግጭት ለመግባት ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነገሮች እንዲፈቱ ለማድረግ ነው ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ በሚኖረው ግዜ ውስጥ በርካታ ስራዎችን መስራት የሚያስችሉ ንጣፎችን የምናበጅበት፣ በርከት ያሉ አስቸኳይ ጉዳዮችን ተደራሽ የምናደርግበት በዋናነት ግን ለቀጣይ የመልሶ ግንባታ ስራዎች አስተማማኝ መሰረት የምናስቀምጥበት ይሆናል ሲሉ ተደምጠዋል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.