አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5 2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ባካሄደው ስብሰባ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃና በቀጣይነት መቀነስ ያስችላሉ ያላቸውን የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት ባንኩ በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የክሬዲት/የባንክ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንዲገደብ የተወሰነ ሲሆን ሁሉም ንግድ ባንኮች የብድር ዕድገት ዕቅዳቸውን በዚህ የብድር ጣሪያ መሠረት እንዲያስተካክሉ ይደረጋል ብሏል፡፡
ቁልፍ የሆኑ የወጪ ንግዶች ላይ የተሰማሩ ላኪዎች የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከዚህ ቀደም ስራ ላይ የነበረው 70/30 የድርሻ ክፍፍል ወደ 50/50 እንዲሻሻል ይደረጋል ያለው ብሔራዊ ባንኩ ላኪዎች 50 በመቶውን ለብሄራዊ ባንክ እንዲያስገቡ፣ 10 በመቶውን አብረው ለሚሰሩት ባንክ እንዲሰጡ እና 40 በመቶውን ለራሳቸው እንዲጠቀሙ ተወስኗል ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
ለመንግስት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው አመት ከተሰጠው ከ1/3ኛ እንዳይበልጥ እና ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአስቸኳይ ጊዜ የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል ይደረጋል ነው የተባለው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት መጨረሻ የዋጋ ንረቱ ከ20 በመቶ በታች እንዲሆንና በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ ማቀዱን በመግለጫው ገልጧል፡፡
የዋጋ ንረት ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያ ከባድና የረጅም ጊዜ የማክሮ ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል ሲል የገለጸው ባንኩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ሕዝቡ ለረጅም ዐመታት በዋጋ ንረት ውስጥ ኖረዋል፣ ባለፉት አስር ዓመታት የዋጋ ንረቱ በአማካይ በዓመት 16 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል፡፡አስ