ዜና፡ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉር አራት ወራት ጥሎት የነበረውን የኢንተርኔት ገደብ አንስቷል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 11 / 2015 ዓ.ም፡- ጥር ወር መገባደጃ በመንግስት እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርትቲያን መካከል በተፈጠረ እሰጥ አገባን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በተወሰቡ ማህበራዊ መገናኝ ዘዴዎች ላይ ጥሎት የነበረውን ገደብ ከአራት ወር በኋላ አንስቷል፡፡

መንግስት ፌስቡክ፣ ቴልግራም፣ ቲክቶክን ጨምሮ በሌሎች ማህበራዊ መገናኛ መተግበሪያዎች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሉ ተጠቃሚው በቪፒኤን መተግበሪያን በመጠቀም ገደብ የተጣለባቸውን ማህበራዊ መገናኝ ዘዴዎች  ሲጠቀም መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በትላንትናው እለትም ይህ ገደብ መነሳቱ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በኢንተርኔት ላይ የጣለውን ደገብ እንዲያነሳ በርካታ የሀገር ውስጥና  የውጭ ተቋማት ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ተቋም የሆነው ሲፒጄን ጨምሮ 47 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግስት ኢንተርኔት በመዝጋት የሚያደርገውን አፈና ያቁም ሲሉ ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ መጠየቃቸውም ይታወሳል። የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ያልተገደበ የኢንተርኔት እና የዲጂታል ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የማግኘት መብትን ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው አሳስበዋል።

መንግስት ኢንተርኔትን በመዝጋት እንደመሳሪያ እየተጠቀመበት ይገኛል ሲሉ ስጋታቸውን በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት ድርጅቶቹ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በሀገሪቱ አገልግሎቶቹ የተቋረጡበትን ሁኔታ በማሳያነት አቅርበዋል። ኢንተርኔት አገልግሎትን መዝጋት መሰረታዊ የሰብአዊ መብትን መጋፋት እና የጋዜጠኞችን መብት እና ደህንነትን ማሳጣት ነው ሲሉ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው ሞግተዋል።

የካቲት 30 ቀን 2015 አለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ ጠይቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ መንግስት ገደቡን እንዲያነሳ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሃላፊው ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ እና  የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበዋል። በቅርቡ ኢትዮ ቴሌኮም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አካላት ተመሳሳይ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገደቡን የማንሳት ሃላፊነት የመንግስት ነው በማለት ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.