ዜና፡ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ የመውጫ ፈተና ላይ የተነሳውን ጥሬታ ተከትሎ ትምህርት ሚኒስቴር ተመሳሳይ ያለሆነ እና ለከፊል ተማሪዎች ብቻ የጨመረው ነጥብ ሌላ ቅሬታን አስነሳ

አዲስ አበባ፣ ሓምሌ 14 /2015 ዓ.ም፡- የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ “የመውጫ ፈተና እንዲመረመርና ተገቢው ማሻሻያ እንዲደረግ የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍሎች እየጠየቁ ይገኛሉ። ተቋማቱ ለተማሪዎች የተሰጠው ፈተና ተማሪዎቹን የማይምጥን በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች በመውደቃቸው ቅሬታ እያሰሙ ባለበት ወቅት ትምህርት ሚኒስቴር ተመሳሳይ ያለሆነ እና ለከፊል ተማሪዎች ብቻ የጨመረው ነጥብ ሌላ ቅሬታን አስነስቷል፡፡

ለአዲስ ስታንዳርድ ቅሬታቸውን ያደረሱ ተማሪዎች እንደሚገልፁት  “የተጨመረው ውጤት በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ተማሪዎች ድጋሚ እንፈተን የሚለውን ጥያቄ ለመቀልበስና በሚዲያ የሚናፈሰውን ዜና ዝም ለማስባል ብሎም በሚዲያ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ የማዘጋጀትና ራስን ከተጠያቂነት ነፃ አውጥቶ ነገሩን ትኩረት በማሳጣት ሀሳባችንን የማኮላሸት አለማን ያነገበ በሴራ የተሞላ እቅድ ነው” ብለዋል።

ተማሪዎቹ አክለውም፣ የእርማት ስህተት ነው ተብሎ ጥቂት የተጨመረው  ነጥብ፣ “እንደገኛ እንፈተን” የሚለውን የተማሪዎችን የህብረት ጥያቄ ህብረት እንዲያጣና ተፅዕኖ መፍጠር እንዳይችል ህብረቱን የማፍረስ ማወናበጃ ሀሳብ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል የራሱ ስህተት የሆነውን የፈተና አወጣጥ ለመሸፋፈን እየጣረ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ሁሉንም ፈተና እንዲያርም የተዘጋጀው የ ሶፍትዌር ሲስተም አንድ አይነት ሆኖ በትምህርት አይነቱ የተስካከለ በመሆኑ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርትን ብቻ አሳስቶ የሚያርም ሰው ሰራሽ አስተውሎት( Artificial Intelligence ) ሊኖር እይችልም ብለዋል፡፡

በተጨመረውም ነጥብ ከወደቁት ተማሪዎች ውሰጥ የተወሰኑትን እንዲያልፉ ካደረጉ በኋላ ቢያንስ ከሌሎች አናሳ አላፊ ተማሪዎች ካሉባቸው የትምህርት አይነቶች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ያለፈ ተማሪ እንዳለው በማስመሰል ባጋጣሚ የተከሰተ አርገው በማስመሰልና በማቅረብ በገሀድ የሚታየውን ልዩነት አጥብበው የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ፈተና በትክክልም ችግር ነበረው የሚለውን እይታ ለማደብዘዝና ትኩረት እንዳይሰጠው ለማረግ የታቀደ አሰራር ነው ሲሉ ተመራቂዎቹ ጥሬታ አቅርበዋል።

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲነግ ትምህርት ክፍል ተመራቂ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለፀው ፈተናው ተማሪውን የማይመጥንና እንድንዘጋጅበት ከተነገረን ውጭ መውጣቱን ገልፆ ተማሪዎችን ለመጣል የተደረገ አሰራር ነው ሲል ገልጧል፡፡

ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ ተብለው የሚጠበቁ ጎበዝ ተማሪዎች ሳይቀሩ ፈተናውን መውደቃቸውን የገለፀው ተማሪው ከፈተናው አወጣጥ በተጨማሪ እርማት ላይም ስህተት መኖሩን ከውጤት አሰጣጥ መረዳት ይቻላል ብሏል፡፡

ሓምሌ 12 ቀን ትምህርት ሚኒስቴር ምንም ሳያሳውቅ ለአንዳንዶች ተማሪዎች የማርክ ጭማሪ አድርጓል ያለው ተማሪው ለአንዳንዶች ደግሞ ቀድሞ ያመጡትን ውጤት ቀንሶባቸዋል ሲል ተናግሯል፡፡ ጭራሽኑ ያልተጨመረላቸውን ተማሪዎች መኖራቸውንም ገልጾ የተጨመረው ማርክም እኩል አለመጨመሩን አስረድቷል፡፡

የበርካታ ተማሪዎች ውጤት 29፣37 እና 40 ነው የሚለው ተመሪው ይህ ተመሳሳይ ውጤት ስህተት እነዳለ የሚያመላክት በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሄ ይፈልግልን ሲል ጠይቋል፡፡

ተማሪውን የማይመጥን ተፈና በማውጣት የተማሪን ልፋትና እጣ ፈንታ ገደል በመክተታቸው እጅግ አዝኖናል ሲል ገልጾ ትምህርት ሚኒስቴር ተገቢውን ማስተካከያ እስኪያደርግ ጥያቄያችን ይቀጥላል ብሏል፡፡

ሌላኛው በሀዋሳ ከተማ በግል ኮሌጅ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ተፈታኝ የሆነው አስፋው ደሪሳ ፈተናው የእኛ ያልሆነና ያልተማርናቸውን ጥያቄዎች ነው የያዘው ሲል ገልፆ በዚህ የተነሳ ከዲፓርትመንቱ ያለፈ ተማሪ የለም ሲል ተናግሯል፡፡ 43 በመቶ ይወጣበታል ከተባለው ኮርስ 3 ጥያቄም አልወጣውም ሲል አክሎ የገለፀው አስፋው የወጡት ጥያቄዎች በሙሉ ቀጥተኛ በለመሆናቸው ብዙ ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸውንም አንስቷል፡፡

“ከ30 በላይ ጥያቄዎች ከሌላ ዲፓርትመንት የወጡ ናቸው፣ ተማሪው በዚህ ልክ ሊወድቅ የቻለው በራሱ ድክመት ሳይሆን ያልተማረውን በማውጣታቸው ስለሆነ መፍትሄ ይሰጠን” ሲልም ጠይቋል፡፡ የተጨመረውን ነጥብ በተመለከተም ለእንሱ ኮሌጅ ምንም አይነት ነጥብ አለመጨመሩን ተናግሯል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ከፍተኛ ቅሬታ ከነሱት ተቋማት አንዱ የሆነው የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ፈተናው የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ውጭ የሌላ ማለትም የኮዖፖሬቲቭ አካውንቲን እና ኦዲቲነግ መሰረት ያደረገ ነው ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ሚኒስቴር ያስቀመጠው ኮርሶች በፈተናው አለመካተታቸውን ገልጧል፡፡ ከ15 ኮርሶች ውስጥ ፈተናው ላይ የተካተተው 4 ኮር ብቻ ላይ ትኩረት ማድረጉ ከፍተኛ ቅሬታን አስነስቷል፡፡

በርካታ ጥያቄዎች እያንዳንዳቸው ከ30 ደቂቃ በላይ የሚወስዱ፣ የጥያቄ አወጣጡም የተንዛዛና ረጃጅም በመሆኑ በርካታ ተማተሪዎች እንዲወድቁ በማድረጉ ፈተናው በድጋሜ እንዲታይ የትምህርት ክፍሉ ጠይቋል፡፡

የደባርቅ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል በበኩሉ ፈተናው ላይ የተካተቱት ከ50 በመቶ በላይ ጥያቄዎች የሌላ ዲፓርትመንት ጥያቄዎች መሆናቸውን ገልፆ ይህም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሳይሆን ሆን ብሎ ተማሪዎችን ለመጣል በሚመስል የተዘጋጀ ነው ብለን እንድናምን ተገደናል ብሏል፡፡

አክሎም የፈተናው ጥያቄና ተማሪዎች እንዲዘጋጁበት ተብሎ በትምህርት ሚኒስቴር ከተሰጠው ብሉ ፕሪንት ጋር ፈፅሞ የማይመሳሰል በመሆኑ መፍትሄ ይሰጥ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴርን ምላሽ ለማካተት የደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.