ዜና፡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር በሎስአንጀለስ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3/2015 ዓ.ም፡- የአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካን መንግስት ልዩ ልዑክ የሆኑት ማይክ ሀመር በአሜሪካ በካሊፎርንያ ሎስ አንጀለስ ከተማ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ ተገለጸ። ማይክ ሀመር በዛሬው እለት ወደ ካሊፎርንያ በማቅናት ለዘጠኝ ቀናት በሚኖራቸው ቆይታ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ያወጣው መረጃ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም በትግራይ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት እንደሚወያዩ ተጠቁሟል። በሎሳንጀለስ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ በተለይም ከኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራይ እና ሶማሌ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ያወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአፍሪካ ቀንድ የሴቶች አንድነት የተባለ በቀጠናው የሚገኙ ሴት መሪዎች ቅንጅት ባዘጋጀው በቦብ ሆፕ ፓትርየቲክ አዳራሽ ላይ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል። ስብሰባው ትኩረት የሚያደርገው ሰላም በማጎልበት እና የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ ዙሪያ መሆኑን ተጠቁሟል። አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.