አዲስ አበባ፣ ታህሳሳ 3/ 2015 ዓ.ም፡- በክልሉ ድንበር አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤሕነን) ታጣቂ ቡድን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ጋር በሱዳን ካርቱም ከተማ የሰላም ስምምነት በመፈራረም ታህሳስ 02/2015 ዓ.ም. ወደ ክልሉ መግባቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት አስታወቀ።
ሁለቱ አካላት በደረሱት የሰላም ስምምነት መሠረት የቤሕነን ታጣቂ ቡድን አባላት ትጥቃቸውን ፈትተው ተሃድሶ በመውሰድ በክልሉ የሰላም እና የልማት ሥራዎች ላይ ለመሰማራት ወደ ክልሉ ተመልሰዋል ተብሏል።
የቡድኑ አባላት ከሱዳን ድንበር ሸርቆሌ ወረዳ ገመድ ቀበሌ ጀምሮ ወደ ክልሉ ሲገቡ በአሶሳ ዞን የሸርቆሌ፣ የመንጌ የሆሞሻ፣ የዑራ፣ የአሶሳ እና የባምባሲ ወረዳ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ስምምነቱን ተከትሎም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ከታጠቂ ቡድኑ ጋር የተደረሰው የሰላም ስምምነት የክልሉ መንግስት በተደጋገሚ ለታጠቂ ቡድኖች ያቀርብ የነበረው “የሰላም ጥሪ” ፍሬ ማፍራቱን ማሳያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ልዩነቶችን በመነጋገርና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ አባላቱ የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ በክልሉ በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ታጠቂዎች መሪ አብዱልወሃብ መህዲ ኢሳ፣ በበኩላቸው ህዝቡ ለሰላም የሰጠውን ዋጋ መረዳታቸውን ገልፀው ከመንግስት ጋር በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በክልሉ የሚገኙ ሁሉም ህዝቦች በሁሉም ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል። መወነጃጀልን በማቆም ለጋራ ልማትና ዕድገት መስራት ከሁሉም እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት እና በክልሉ ታጥቆ ሲንቀሳቀስ የነበረው የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የሠላም ስምምነት ጥቅምት 09/2015 ዓ.ም በአሶሳ ከተማ መፈራረማቸው ይታሳል።
በወቅቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ሰምምነቱ ህገ-መንግስቱን ባከበረ መንገድ በውይይት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም እስካሁን የተከፈለው ዋጋ በቂ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፣ ለሠላም ሲባል ከክልሉ መንግስት ጋር በተደረገው ስምምነት እጅግ መደሠታቸውን ገልፀው በውይይት ላይ የተመሠረተ ልማት እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
የሠላም ስምምነቱ በትክክል እስከታች ወርዶ ለክልሉ ሠላም ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም እንዲተባበር አቶ ግራኝ ጥሪ አቅርበው ነበር። አስ