አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4/2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ በተካሄደው ስለሱዳን ጉዳይ በመከረው የኢጋድ የመሪዎች ስብሰባ የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙ ተጠየቀ። ኢጋድ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ሁለቱም ሀይሎች ውጊያቸውን እንዲያቆሙና ባፋጣኝ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲፈጽሙ ጠይቋል።
በተመሳሳይ ኢጋድ በሱዳን የአባል ሀገራቱ ወታደሮች ወደ ሱዳን እንዲገቡ እና ንጹሃንን እንዲታደጉ ለማድረግ ሃሳብ ማቅረቡን ዘገባዎች አመላክተዋል። የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ሃይል ወደ ሱዳን እንዲገባ እና የሰብአዊ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተሰብስበው እንዲወስኑ ለማድረግ በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ከስምምነት መደረሱን ዘገባዎቹ አስታውቀዋል።
የሱዳን ወታደራዊ ሀይሎች በጉባኤው ላይ ባለመሳተፋቸው የተሰማውን ቅሬታ ኢጋድ በትላንትና መግለጫው አመላክቷል።
በሌላ ዜና የሱዳኑ ዳባንጋ ሬዲዮ ባሰራጨው ዘገባ ከኢጋዱ የአዲስ አበባ ጉባኤ ቀደም ብሎ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሱዳን የሲቪል ፖለቲካ ሀይሎች ልዑካንን ተቀብለው ማነጋገራቸውን አስታውቋል። ልዑካኑ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከሚገኙ የሱዳን ተወካዮች፣ ከቀጠናው እና አለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር መምከራቸውን አመላክቷል። ከሁሉም አካላት ጋር ባካሄድነው ምክክር የሱዳን ጦርነት በፍጥነት መቆም እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሰናል ሲሉ የሉዑካኑ አባላት መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል።
በሱዳን የተከሰተውን ቀውስ በዲፕሎማሲ ለመፍታት በአዲስ አበባ የኢጋድ ጉባኤ በበትላንትናው እለት ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል። ጉባኤውን የመሩት ያሉት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሲሆኑ የሱዳን ሀይሎች የኬንያን መሪነት አንቀበለውም ማለታቸው ተዘግቧል። በኢጋድ ከተሰየሙት አሸማጋዮች በተጨማሪ የአሜሪካን መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሃላፊ ሞሊ ፊም በጉባኤው ላይ መገኘታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ማስታወቁነ በዘገባችን አካተናል።
በጉባኤው ላይ ኤርትራ እንደማትሳተፍ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ገልጸውልኛል ሲሉ የሱዳን ላዕለዋይ ምክር ቤት ምክትል ማሊክ አጋር መናገራቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ድረገጽ ዘግቧል። አስ