ዜና፡ የህጻናት አድን ድርጅት ግጭት በተቀሰቀሰበት አማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ

በዋግህምራ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች– ፎቶ- አሚኮ/ ከፋይል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4 /2015 ዓ.ም፡- የህጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) በመንግስት ፀጥታ ሀይልና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት በተቀሰቀሰበት አማራ ክልል ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲቀጥል ጥሪ አቀረበ፡፡

በኢትዮጵያ የህጻናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር ዣቪየር ጆበርት ለሁለት አመታት የዘለቀው ግጭት በስምምነት ከተቋጨ በኋላ በአማራ ክልል እያጋጠመ ባለው አሳሳቢ ግጭት የህፃናትና የቤተሰቦች ሕይወት አደጋ ላይ ወድቋል ብለዋል፡፡

“በቅርቡ የተደረገው ጦርነት ያስከተለው ቁስል ጠባሳ ሳይሻር አሁንም ተደግሟል፤ የህፃናት ህይወት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ ሰብዓዊ ድርጅት ተፋላሚ ፓርቲዎች ለንፁሃን ደህንነት ቅድሚያ እንዲሰጡና በክልሉ የሚገኙ 580 ሺህ ተፈናቃዮችን ጨምሮ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የስብኣዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲደርሳቸው እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ህፃናትን ከረሃብ፣ ከግጭት፣ መፈናቀልና ጥቃት መጠበቅ አለብን፡፡ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ቤተሰቦች ደህንነታቸው እንዲጠበቅላቸው እና አስፈላጊ ሰብአዊ እርዳታን ያለ ምንም እንቅፋት እንዲያገኙ ማድረግ አለብን” ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የህጻናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያ አማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከ60 አመታት በላይ እየሰራ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በጤና፣ በስነ-ምግብ፣ ውሃ እና ፅዳት፣ በትምህርት፣ በጥሬና በአይነት ስርጭት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል፡፡ በ 2022 የህጻናት አድን ድርጅቱ ህይወት አድን የሆኑ ምግቦች፣ የውሃ ስርጭት እና የተመጣጠነ ምግብ ህክም እና በሌሎች አገልግሎቶች ወደ 5.1 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትን ጨምሮ 7.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎችን ድጋፍ ማድረጉን በመግለጫው ገልጿል።አስ

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.