ዜና፡-ወደ ውጭ ሀገር ሊወጣ የነበረ ከ300 ሺህ ዶላር በላይ መያዙን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ

አዲስ አባባ፣ጥቅምት25፣20015፡- በአዳማ ከተማ ከ300 ሺህ ዶላር በላይ ወደ ውጭ ሀገር ለማስወጣት የሞከረ ግለሰብ ከአሽከርካሪው ጋር መያዙን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አሳውቋል።

ግለሰቡ ኮድ 3/89158 ኢ.ት በሆነ ሎቤድ መኪና ገንዘቡን ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በስውር ደብቆ ሲያጓጉዝ መያዙን የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል እንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ ገልፀዋል።

በአዳማ ከተማ ልዩ ቦታው ዳቤ ሶሎቄ በሚባል ኬላ ፍተሻ ላይ የተያዘው የገንዘብ መጠንም 302 ሺህ 400 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን ባለሙያዋ ገልጸዋል።

በብሔራዊ ደህንነት እና በአዳማ ከተማ የፀጥታ ኃይሎች ትብብር ጥቅምት 23፣ 2015 ዓ.ም ላይ የተያዘው ይህ ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር በሚጓዝ የኮንቴይነር ጭነት ስር በስውር ቦታ ተደብቆ እንደነበር ምክትል ኢንስፔክተሯ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥቅምት 16፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብን ከ25 ግብረአበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራባቸው መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡

No comments

Sorry, the comment form is closed at this time.